በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው ዓለም አቀፍ የመጽሐፍት ድርጅቶች የመጻሕፍት ሽያጭና ግብይት በአዲስ አበባ ሊደረግ ነው

103

ሰኔ 4/2014/ኢዜአ/ የ'ቢግ ባድ ዎልፍ' እና 'ሻርዣ' የተሰኙት የዓለማችን ስመ-ጥር የመጽሐፍት ድርጅቶች የመጻሕፍት ሽያጭና ግብይት መድረክ በአዲስ አበባ ሊያካሂድ መሆኑን የመርሃ-ግብሩ አስተባባሪ የፀሐይ አሳታሚ ድርጅት አስታወቀ።

በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ከጥንት እስከ ዛሬ ከምዕራብ ዘመም ኅይላት ጥርስ ለተነከሰባት አገራቸው በየዘመናቸው ሲሞግቱላትና ለሕልውናዋ ዘብ ሲቆሙላት ማየት አዲስ ነገር አይደለም።

ውልደትና ዕድገቱ አዲስ አበባ የሆነው ኤልያስ ወንድሙ ኢትዮጵያን በልኩ እንዲያፈቅር፣ ለጥቅሟና ክብሯ ዘብ እንዲቆም፣ ለታሪኳ ትንሳኤ እና ከፍታዋ እንዲተጋ መሰረት የሆነው አስተዳደጉ እንደሆነ ይናገራል።

ኢትዮጵያዊነትን በንባብ ሳይሆን ተወልዶ ባደገበት ሰፈር፣ ቤተሰብና አካባቢ ከነበረው ማኅበረሰባዊ ስብጥርና ማኅበራዊ ክዋኔ የተኖረ ማንነት እንደሆነ የሚተርከው ኤልያስ፤ የዛሬ ማንነቱ የተቀረጸው ከመሰረቱ መሆኑን ይገልጻል።

የቀዶ ጥገና ሐኪም የመሆን የልጅነት ሕልም ቢሰንቅም በዘመኑ ያስተዋለውን የኢትዮጵያ ማህበረ-ፖለቲካ ሕፀፅ ይነቅስና ይጠግን ዘንድ ሙያውን ለጋዜጠኝነትና ማኅበረሰብ አንቂነት ሰጥቶ ስለኢትዮጵያ ድምጹን እንዲያሰማ አስገድዶታል።

ለኢትዮጵያ ወግኖ መንቀሳቀሱ በፖለቲካው ያልተወደደለት ኤልያስ ከሩብ ምዕተ-ዓመት በፊት ወደ ውጭ እንዲሰደድ ቢገደድም፤ ኢትዮጵያን ለማገልገልና የቁርጥ ቀን ልጅነቱን ለማሳየት ግን ስደት አልበገረውም።

በወላጅ እናቱ ስያሜ እና ለእናት አገሩ ትዕምርትነት በማሰብ 'ፀሐይ' በሚል በመሰረተው አሳታሚ ድርጅት ዛሬ ላይ በአገረ-አሜሪካ በሕትመት ጥራቱ የተመሰከረለት የዕውቀት ማዕድ ሆኖ ስኬታማ ሥራዎች እየከነወ ነው።

ፀሐይ አሳታሚ ድርጅት የተዛባን ምዕራብ ተኮር ትርክትና ሴራ በመንቀል፣ የኢትዮጵያን ሐቆች በመግለጥ እና በሕትመት ችግር የተጋረደውን የኢትዮጵያን ታሪክ የሕትመት ፀሐይ እንዲያገኝ የሚያስችሉ ሥራዎችን ከማበርከቱ ረገድ አይተኬ ሚና ተጫውቷል።

ከዚህም ባሻገር ለኢትዮጵያዊያን ፀሐፍትና ጥናትና ምርምር ሥራዎችን ለማሳተም በምዕራባዊያን ተቋማት ዘንድ ዕድል የተነፈጉት ምሁራን እፎይታ እንዲያገኙ በማስቻሉ ለድርጅቱ ባለቤት የሚፈጥረው ደስታ ወደር የለውም።

ኤልያስ ወንድሙ ከፀሐይ አሳታሚ ድርጅት ባለቤትና ሥራ አስፈጻሚነቱ ባሻገር የጥናትና ምርምር ጆርናሎችን በመመስረትና በታዋቂ ጋዜጦች ላይ ኢትዮጵያን የወገኑ፣ ጠላቶቿን የሞገቱ ሃሳቦች በማንጸባረቅም አለኝታነቱን አስመስክሯል።

ከአራት ዓመታት በፊት ደግሞ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ ስመ-ጥሩ የፀሐይ አሳታሚ ድርጅት ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ የዕውቀት ማዕከልነት ተልዕኮውን ለማስፋት የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ ነው።

በመጽሐፍት ሕትመት ረገድ በይዘትም ሆነ በሕትመት ጥራት፣ የሕትመት ግብዓት የሚሆን የውጭ ምንዛሪ እጥረት እና ተያያዥ ችግሮች ለዘርፉ ፈተና በመሆኑ ጠንካራ አሳታሚ ድርጅት እንደሌለ ይገለፃል።

ፀሐይ አሳታሚ ብቻውን የሕትመት ዘርፉን ችግር ባይቀርፍም የበኩሉን ሚና ለመጫወት እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ከራሱ ሕትመቶችን ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ ዓለም አቀፍ ዕውቀትን ወደ ኢትዮጵያ ተደራሽ ማድረግና ትውልድን ከዕውቀት በረሃ የማውጣት አንዱ ትኩረቱ መሆኑን ይገልጻል።

በቅርቡም ዓለም አቀፍ ዕውቀቶችን ኢትዮጵያ ውስጥ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚዳረሱበትን ፕሮጀክት በመቅረጽ፤ በዓለም ላይ በመጽሐፍት ላይ ስመ-ጥር የሆኑ ሁለት ድርጅቶች ጋር መዋዋሉን ገልጿል።

ድርጅቶቹም 1 ሚሊየን መጻሕፍትን ከ55 እስከ 95 በመቶ በሆነ ቅናሽ በአስር ቀናት ውስጥ ለ24 ሰዓታት በመሸጥ በዓለም ላይ በመጽሐፍ ሽያጭ ቀዳሚነት ያለው 'ቢግ ባድ ዎልፍ' እና በዓለም መጽሐፍት መገበያያ መድረክ ዝግጅቱ ከፍራክፈርት ቀጥሎ ሁለተኛ የሚሰኘው 'ሻርዣ ቡክ ፌር' ናቸው።

አቶ ኤልያስም የ'ቢግ ባድ ዎልፍ' መሥራች አንድሩ ያፕ እና 'ሻርዣ ቡክ ፌር' ኃላፊ መሐመድ ኑርን ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት የኢትዮጵያን የመጽሐፍ ኢንዱስትሪ ዘርፍ እድሎች አስጎብኝቷል።

በዚህ ጉዳይ ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር ስለመነጋገራቸውም ተናግሯል።

የድርጅቶቹ ኃላፊዎች በጉብኝቱ እንደተደሰቱበት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የመጽሐፍት አቅርቦት እንጂ የተነባቢነት ዕድሎች ሰፊ መሆናቸውን እንደታዘቡ ገልጿል።

ሁለቱ ድርጅቶች በቀጣይ አምስት ዓመታት በመካከለኛው ምሥራቅና በአፍሪካ 1 ቢሊየን መጻሕፍት ተደራሽ ለማድረግ ግብ የያዙ ሲሆን፤ ከቅርብ ወራት በፊትም በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች 1 ሚሊየን መጻሕፍትን በመሸጥ ስኬታማ ሥራ ማከናወናቸውን አስታውሷል።

በዚህም በአፍሪካ ደረጃ የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የመጽሐፍት ሽያጭና ግብይት መድረክ በአዲሱ ዓመት የመጀመሪያ ወራት በአዲስ አበባ እንዲደረግ መታቀዱን አልያስ ገልጿል።

የድርጅቶቹ ኃላፊዎች ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በታንዛኒያ፣ ኬንያና ኡጋንዳ ጉብኝት ማድረጋቸውን ገልጾ፤ በቅድሚያ 1 ሚሊየን መጻሕፍትን ኢትዮጵያ ውስጥ ለመሸጥ እንደወሰኑ ተናግሯል።

በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል የመጽሐፍት መርሃ-ግብሩ ዕውን እንዲሆን ቀና ትብብር እንዳለ ተገልጾላቸዋልም ነው ያለው።

የመጽሐፍት መድረክ ኢትዮጵያዊያን በአካል ማግኘት የማይቻላቸውን በበይነ-መረብ የሚታዩ መጻሕፍትን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲገዙ የሚያስችል፣ ለመጽሐፍት መደብሮች የአቅርቦት ችግር ለመፍታት ትልቅ ዕድል እንደሆነ ገልጿል።

ዓለም አቀፍ ዕውቀቶችን ሳይገበዩ በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ እኩል መወዳደር እንደማይቻል የሚገልጸው ኤልያስ፤ ፀሐይ አሳታሚ የአገር ውስጥ ፀሐፍት ሥራዎች በጥራት እንዲታተሙ ከማድረግ ባለፈ የዕውቀት ክፍተትን የመሙላት ፕሮጀክት አንዱ አካል እንደሆነ ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም