በክልል ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች መፍጠር ያስፈልጋል–ቢሮው

4

ዲላ ሰኔ 5/2014 (ኢዜአ) ባለሀብቶችን በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲሳተፉ ምቹ ሁኔታዎች መፍጠር እንደሚገባ የደቡብ ክልል ኢንቨስትመንትና ኢንዲስትሪ ልማት ቢሮ አስታወቀ ።

በደቡብ ክልል በጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ “ኢትዮጵያ ታምርት” በሚል መሪ ሀሳብ የኢንቨስትመንት ፎረም ዛሬ አካሂዷል።

የደቡብ ክልል ኢንቨስትመንትና ኢንዲስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ሐልጌዮ ጂሎ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት የተያዘውን የብልጽግና ግብ በአጠረ ጊዜ በማሳካት የዜጎች ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የኢንቨስትመንት  አመራጮች  መጠቀም ይገባል።

በተለይም በርካታ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር የሚችሉ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ ባለሃብቶች እንዲሳተፉ ምቹ ሁኔታዎች መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል።

የአከባቢን ሰላም በማስጠበቅ ፣መሰረተ ልማቶችን በማሟላትና ለባለሃብቶችን አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ምቹ  ሁኔታዎችን መፍጠር እንደሚገባ ተናግረዋል።

በክልሉ በተያዘው በጀት ዓመት ለዘርፉ በተሰጠው ትኩረት ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ ኢንቨስትመንቶችን መሳብ መቻሉን ጠቅሰው ይህም ዘርፉ እየተነቃቃ መምጣቱን የሚያመላክት ነው ብለዋል።

በቀጣይም ዘርፉን አጠናክሮ ለማስቀጠል የአገልግሎት አሰጣጥ ማዘመን ላይ ማተኮር እንደሚገባ  አስገንዝበዋል።

“በክልሉ የሚስተዋለውን ባለሃብት የማጉላላት፣ ግልጽ መረጃ ያለመስጠትና መሰል የመልካም አስተዳደር ችግሮችና ብልሹ አሰራሮችን መቅረፍ ይገባል” ሲሉ ጠቁመዋል።

የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዮት ደምሴ በበኩላቸው በዞኑ ከኢንቨስትመንት ዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳካት መሬት ከማቅረብ ባለፈ መሰረተ ልማቶችን የሟሟላት ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ለተሰማሩ ባለሃብቶች ጥራት ያለውና ተወዳዳሪ ምርትና አገልግሎት በመስጠት ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዞኑ ባለፉት 11 ወራት ከ140 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 25 ባለሃብቶች በኢንዲስትሪ፣ ግብርናና አገልግሎት ዘርፎች የኢንቨስትመንት ፍቃድ በመውሰድ ወደ ስራ መሰማራታቸውን የገለጹት የዞን ኢንቨስትመንትና ኢንዲስትሪ ልማት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አክሊሉ በደቻ ናቸው ።

በዚህም ለ2 ሺህ 246 ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል መፍጠር መቻሉን አስረድተዋል።

ባለሃብቶች በዞኑ በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች በመሰማራት እራሳቸውና ሀገርን እንዲጠቅሙ ጥሪ አቅርበዋል።

ዛሬ የተካሄደው ፎረም በዘርፉ ያሉትን ተግዳሮቶችን መፍታት የሚያስችል አቅጣጫ በማስቀመጥ ኢንቨስትመንቱን ለማነቃቃት ያለመ መሆኑን ጠቅሰዋል

በሆቴልና ሎጅ ስራ መስክ የተሰማሩት አቶ ዮሴፍ ብርሃኑ እንዳሉት የአገልግሎት ዘርፍ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝና በጸጥታ ችግር በተደጋጋሚ ለጉዳት የተዳረገ ቢሆንም በተደረገው ጥረት መሻሻሎች ማሳየቱን  ጠቅሰዋል።

በከተማው በሚስተዋሉ የመንገድና የኤሌክትሪክ መቆራረጥ በስራቸው ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደረ በመሆኑ ችግሩ እንዲፈታላቸው ጠይቀዋል።

በግብርና ምርቶች ላይ የሚስተዋለው ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ላይ የሚመለከታቸው አካላት ቁጥጥር እንዲያደርጉ ጠቁመዋል።

በመድረኩ በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ተሰማርተው የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ ባለሃብቶች የዋንጫና የሰርትፍኬት ሽልማት የተሰጠ ሲሆን የመስክ ጉብኝትም ተካሂዷል።