ሀገር በቀል የሽምግልና እሴቶችና ሃይማኖታዊ አስተምህሮችን በማጠናከር ለዘላቂ ሰላም በጋራ እንስራለን

3

ጎንደር ሰኔ 5/2014 (ኢዜአ) ”ሀገር በቀል የሽምግልና እሴቶችና ሃይማኖታዊ አስተምህሮችን በማጠናከር ለከተማችን ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ በጋራ እንስራለን” ሲሉ የጎንደር ከተማ የሃገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ተናገሩ፡፡

የከተማዋ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ከአማራ ክልል ርዕስ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ጋር በሰላም ጉዳይ ዛሬ በጎንደር ከተማ መክረዋል።

በመድረኩ ከተሳተፉት የሃይማኖት አባቶች መካከል ሃጂ ማሩፍ አሊ የከተማዋን ሰላምና ልማት የማይሹ የጥፋት ሃይሎች በተለያዩ ጊዜያት በማንነትና በሃይማኖት ሽፋን ህዝቡን በማጋጨት እኩይ ዓላማቸውን ለማስፈጸም ያደረጉት ሙከራ መክሸፉን ተናግረዋል።

“ሁለቱ ሃይማኖቶች ተጋጭተው አያውቁም፤ ሆኖም የከተማዋን ስም  ለማጉደፍ ሌት ተቀን ሴራ ሲሸርቡ የነበሩ ሃይሎች መጠቀሚያ አድርገውናል፤ ይህም ትምህርት ሊሆነን ይገባል” ሲሉ ገልጸዋል።

“ሃይማኖታዊ አስተምሯችን ወንድም ወንድሙን እንዲገድልና እንዲያፈናቅል አይፈቅድም” ያሉት ደግሞ ቄስ መንክር አለሙ ናቸው፡፡

“ክርስትናና እስልምና የሚይነጣጥሉንና የሚያጋጩን ሊሆኑ አይገባም፣ ለዚህም የቀደመ አብሮነታችንና አንድነታችን መልሰን የከተማችንን ሰላም በጋራ እናረጋግጣለን” ሲሉም አክለዋል።

የሀገር ሽማግሌው አቶ ባዩህ በዛብህ በበኩላቸው ” በአብሮነትና በመከባበር ዘመናት የተሻገሩትን የሁለቱ ሃይማኖቶች መልካም እሴቶችን በማስቀጠል በኩል የሃገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች የጋራ ሃላፊነት አለብን” ብለዋል።

የተዛቡ መረጃዎችን በማራገብ ትውልድ እንዲገዳደል መፍቀድ እንደማይገባ ገልጸው፣ “በሰከነ መንገድ ችግሮችን በውይይትና በመመካከር በመፍታት ለህዝብ አስተማማኝ ሰላም ለማረጋገጥ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

“የህግ ማስከበር ሥራው ለከተማችን ሰላምና እፎይታ አስገኝቶልናል፤ በተለያዩ በቁጥጥር ስር የዋሉ ወንጀለኞች በህግ አግባብ እንዲጠየቁ እንፈልጋለን” ያሉት ደግሞ ሌላው የመድረኩ ተሳታፊ አቶ አህመድ መሃመድ ናቸው።

የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘውዱ ማለደ በበኩላቸው የከተማውን ሰላም በማረጋገጥ በኩል የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናገረዋል።

የህግ የበላይነት ለማረጋገጥ የተጀመረው ሥራ ህዝቡን በማሳተፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመው፤ በአሁኑ ወቅት የከተማዋ ሰላም አስተማማኝ በሚባል ደረጃ ማረጋገጥ መቻሉን ገልፀዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ እንዳሉት፣ መንግስት የህዝቡን ሰላምና ደህንነት የማረጋገጥ ግንባር ቀደም ሃላፊነቱን በመወጣት ወንጀለኞችን ለሕግ የማቅረብ ስራውን አጠናክሮ ይቀጥላል።

“አንዴ በብሔር፤ አሁን ደግሞ በሃይማኖት ሊከፋፍሉት የሚፈልጉ ቡድኖችን ህዝቡ አጥብቆ ሊያወግዝና ለህግም አሳልፎ በመስጠት ሰላምና ደህንነቱ ሊያረጋግጥ ይገባል” ሲሉ አስገንዝበዋል።

የክልሉ መንግስት በጎንደር ከተማ በሃይማኖት ሽፋን ተከስቶ በነበረው ግጭት የተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍና መልሶ ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ የሚያስችል  ኮሚቴ በማቋቋም ወደ ስራ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

በግጭቱ እጃቸውን ያስገቡ ቡድኖች በጥፋታቸው ልክ በህግ አግባብ እንዲጠየቁ ለማድረግ መንግስት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፣ ህዝቡም ለህግ የበላይነት መከበር ከመንግስት ጎን እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።

በምክክር መድረኩ ላይ ከ6 ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።