ኮሚሽኑ በመዲናዋ በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ ዜጎች ለሚከናወነው የቤት እድሳት ስራ የሚውል የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

161

ሰኔ 5 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢፌዴሪ ጉምሩክ ኮሚሽን በመዲናዋ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ ዜጎች ለሚከናወነው የቤት እድሳት ስራ የሚውል ከ14 ነጥብ 5 ሚሊዮን በር በላይ ግምት ያለው የቁሳቁስ ድጋፍ አበረከተ፡፡

ድጋፉን የኢፌዴሪ ጉምሩክ ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ ለአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ  አዳነች አቤቤ አስረክበዋል።

ከንቲባዋ በዚሁ ጊዜ፤ የግብዓት እጥረት በመዲናዋ የሚከናወኑ የልማት ሰራዎቸን እየፈተነ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

በአብዛኛው ጊዜ የግብዓት እጥረት የሚፈጠረው በህገ-ወጥ መልኩ ህዝብን ዘርፈው ለመክበር በሚጥሩ አካላት መሆኑን ጠቅሰው፤ የጉምሩክ ኮሚሽን ህገ-ወጥነትን በመከላከል ረገድ የሚጠበቅበትን ሚና እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽኑ በአንድ በኩል ህገ-ወጦችን በመታገል በሌላ በኩል ደግሞ የህዝብን ሃብት ለህዝብ ጥቅም እያዋለ መሆኑን አንስተው፤ ዛሬ ያደረገው ድጋፍም በዚህ ረገድ ተጠቃሽ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽኑ ላደረገው ድጋፍም ከንቲባዋ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ድጋፉ ከተማ አስተዳደሩ በመዲናዋ በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል የሚያከናውነውን ተግባር በማሳለጥ ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡

ሌሎች ተቋማትም የኮሚሽኑን ተግባር አርአያ በማድረግ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ በበኩላቸው ኮሚሽኑ ድጋፍ ያደረገው  በኮንትሮባንድ ሲንቀሳቀሱ በቁጥጥር ስር ያዋላቸውን ቁሳቁሶች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የከተማዋ አስተዳደሩ የነዋሪዎችን  ህይወት ለመቀየር የሚያደርገውን ጥረት አድንቀው፤ ከዚህ አኳያ ኮሚሽኑ ከሳምንት በፊት በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ለሚታደሱ የአቅመ ደካማ ዜጎች መኖሪያ ቤቶች ግንባታ የሚውል  15 ሚሊዮን ብር  ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

ሌሎች ተቋማትም በከተማዋ የዜጎችን ኑሮ ለመቀየር እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን እንዲደግፉም ነው ኮሚሽነሩ ጥሪ ያቀረቡት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም