ኢትዮጵያ በአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና አምስተኛ ደረጃ ይዛ አጠናቀቀች

2

ሰኔ 5 ቀን 2014 (ኢዜአ)ኢትዮጵያ በሞሪሺየስ በተካሄደው 21ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና አምስተኛ ደረጃ ይዛ አጠናቃለች።

ከሰኔ 1 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በኮት ዶአር ናሽናል ስፖርት ኮምፕሌክስ ስታዲየም ሲካሄድ የቆየው ሻምፒዮና ዛሬ ተጠናቋል።ኢትዮጵያ በአራት የወርቅ፣ስድስት የብር እና አራት የነሐስ በድምሩ 14 ሜዳሊያዎች በማግኘት አምስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

ዛሬ በሻምፒዮናው ማጠናቀቂያ በተደረጉ የፍጻሜ ውድድሮች ኢትዮጵያ በ5 ሺህ ሜትር ወንዶች በአትሌት ኃይለማርያም አማረ እንዲሁም በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል ሴቶች በአትሌት ወርቅውሃ ጌታቸው አማካኝነት ሁለት የወርቅ ሜዳሊያ አግኝታለች።

በተጨማሪም ሁለት የብርና ሶስት የነሐስ ሜዳሊያዎችን ማግኘት ተችሏል።አትሌት ኃይለማርያም አማረ በ5 ሺህ ሜትር እና በ3 ሺህ ሜትር ወንዶች መሰናክል በማሸነፍ ሁለት የወርቅ ሜዳሊያ አግኝቷል።

ኢትዮጵያ በውድድሩ የመጀመሪያ የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘችው በ10 ሺህ ሜትር ወንዶች ፍጻሜ በአትሌት ሞገስ ጥዑማይ አማካኝነት ነው።በሻምፒዮናው 28 ሴት እና 26 ወንድ በድምሩ 54 አትሌቶችን ተሳትፈዋል።

ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2018 በናይጄሪያ አሳባ በተካሄደው 21ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና 2 የወርቅ፣ሶስት የብርና አምስት የነሐስ በድምሩ 10 ሜዳሊያዎች በማግኘት አራተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው።

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በተካሄዱት 21ዱም የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ተሳትፋለች።