የገርጂ የመኖሪያ መንደር ግንባታ ፕሮጀክት ቴክኖሎጂን በመጠቀም የመኖሪያ ቤት እጥረትን በአጠረ ጊዜ መቅረፍ እንደሚቻል ትምህርት የሚሰጥ ነው

286

ሰኔ 05 ቀን 2014 (ኢዜአ) የገርጂ የመኖሪያ መንደር ግንባታ ፕሮጀክት ቴክኖሎጂን በመጠቀም በከተሞች ያለውን የመኖሪያ ቤት እጥረት በአጠረ ጊዜ መቅረፍ እንደሚቻል ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ረሻድ ከማል ተናገሩ፡፡

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽ በቀበና እና ገርጂ ሳይት ያስገነባቸውን የመኖሪያ ቤት ፕሮጀክቶች ያስመረቀ ሲሆን፤ በተለይ በገርጂ ሳይት የተመረቀው የመኖሪያ መንደር በኢትዮጵያ አዲስ የግንባታ ቴክኖሎጂን ያስተዋወቀ ፕሮጀክት ነው፡፡

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር-ቤት አባላትና አምባሳደሮች ተገኝተዋል።

ኮርፖሬሽኑ በገርጂ ሳይት ባስገነባው የመኖሪያ መንደር "አልሙኒየም ፎርምወርክ" የተሰኘ ዘመናዊ የግንባታ ቴክኖሎጂን ጥቅም ላይ ማዋሉን የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ ራሻድ ከማል ተናግረዋል።

ኢትዮጵያዊያን ሙያተኞች ቴክኖሎጂውን በማላመድ ግንባታውን በፍጥነት፣ ጥራትና በተያዘለት ጊዜ ያከናወኑበት መሆኑም ነው ተናግርዋል።

ኮርፖሬሽኑ ይህን ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ በማዋልም በገርጂ የመኖሪያ መንደር አስር ወለል ያላቸው 16 ህንጻዎችን በ18 ወራት ጊዜ ውስጥ ገንብቶ ማጠናቀቅ  ችሏል ብለዋል።

የመኖሪያ መንደሩ ዘመናዊ የደህንነት ጥበቃ ስርዓት የተገጠመለት፣ ከ800 በላይ መኪና ማቆም የሚያስችል ስፍራ፣ የጋራ መጠቀሚያ አዳራሽ፣ የተለያዩ ስፖርት መስሪያ ቦታዎች፣ ካፌና ሬስቶራንት፣ መናፈሻ፣ አምፊ ቴዓትር፣ የልጆች መጫወቻንና መዋኛ ገንዳን ያካተተ መሆኑንም አንስተዋል።

በገለልተኛ አካል በተደረገ ጥናት የመኖሪያ መንደሩ ግንባታ 13 ቢሊዮን ብር ግምታዊ ዋጋ ቢሰጠውም ኮርፖሬሽኑ ግን በሶስት ነጥብ ስልሳ ስድስት ቢሊዮን ብር በሆነ ወጪ ብቻ ግንባታውን ማከናወኑን ነው የጠቀሱት።

በተጨማሪም የግንባታ ፕሮጀክቱ  ዘመናዊ የግንባታ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የከተሞች የመኖሪያ ቤት እጥረትን መፍታት እንደሚቻል ትምህርት የሰጠ እንደሆነም ነው የገለጹት፡፡

ኮርፖሬሽኑ ለ28 ዓመታት ከቤት ግንባታ ስራ ርቆ መቆየቱን ያስታወሱት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ግን ዛሬ የተመረቁትን ጨምሮ በ10 ሳይቶች ላይ የመኖሪያ ቤት ግንባታ እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በቀጣይ ከ3 እስከ 5 ዓመታት ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቁ የቤት ግንባታ ፕሮጀክቶች በአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተሞች በ30 ሄክታር መሬት ላይ እንደሚያካሄድ ገልጸዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊና የኮርፖሬሽኑ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ተፈሪ ፍቅሬ በበኩላቸው ኮርፖሬሽኑ የከተሞችን የመኖሪያ በት ችግር ለመፍታት አርአያ የሚሆን ስራ እየሰራ ነው ብለዋል።

አዲስ አበባን ጨምሮ በከተሞች  ከፍተኛ የቤት ፍላጎት በመኖሩ ምክንያት ሰፋፊ የቤት ግንባታ ስራዎች እንደሚያስፈልጉ ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ መንግስት  በአስር ዓመቱ የልማት እቅድ ውስጥ ከ 4 ሚሊዮን ቤቶች በላይ ለመገንባት ማቀዱን አንስተዋል።

የገርጂ መኖሪያ መንደር ግንባታ የአገር በቀል ኩባንያ በሆነው ኦቪድ ኮንስትራክሽን የተገነባ ሲሆን፤ የዲዛይን አማካሪው ደግሞ የሕንድ አገር ኩባንያ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በፕሮጀክቱ ጥቅም ላይ የዋለው አልሙኒዬም ፎርም ወርክ ቴክኖሎጂ ደግሞ የደቡብ ኮሪያ ምርት እንደሆነ ነው የተገለጸው፡፡

በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን ጨምሮ በግንባታ ሂደቱ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም