የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በምዕራፍ ሶስትና አራት በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተሞች የቤቶች ግንባታ ሊጀምር ነው

328

ሰኔ 5 ቀን 2014 (ኢዜአ)የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በምዕራፍ ሶስትና አራት በአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተሞች የቤቶች ግንባታን በቅርቡ እንደሚጀምር አስታወቀ።

ኮርፖሬሽኑ ያስገነባቸውን የቀበናና የገርጂ ሳይቶች ዘመናዊ የመኖሪያ መንደር ፕሮጀክቶች ዛሬ አስመርቋል።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ ረሻድ ከማል በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤በድርጅቱ ምዕራፍ ሶስትና አራት እቅድ መሰረት በአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተሞች በጥቂት ወራት ውስጥ የቤቶች ግንባታ እንደሚጀመር ገልጸዋል።

ግንባታው በ30 ሄክታር መሬት ላይ ያርፋል።ስራውን ለማስጀመር የሚያስፈልገው የመሬትና ሀብት ማፈላለግ ስራ መጠናቀቁን አመልክተዋል።

በአብዛኛው ግንባታውን ለማስጀመር የሚያስፈልጉ ስራዎች መጠናቀቃቸውን አመልክተዋል።

የቤቶቹ ግንባታ ከሶስት እስከ አምስት ዓመት ለማጠናቀቅ ታቅዷል ብለዋል።የሚገነቡት ቤቶች ሲጠናቀቁ በኢትዮጵያ ያለውን የመኖሪያ ቤቶች ችግር ለመፍታት አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ነው አቶ ረሻድ የገለጹት።

በሁለቱ ከተሞች የሚገነቡ ቤቶች መንግስት በ10 ዓመት እቅዱ በከተማ ቤቶች ልማት ፕሮግራም ለመገንባት ያቀደውን ከአራት ሚሊዮን በላይ ቤቶች የመገንባት እቅድን ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውን ነው አቶ ረሻድ የገለጹት።

ዛሬ የተመረቀው የገርጂ ዘመናዊ የመኖሪያ ቤቶች መንደር 3 ቢሊዮን 66 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገበትም አክለዋል።የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 398/2009 የተቋቋመ የመንግስት የልማት ድርጅት ነው።

ኮርፖሬሽኑ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ቤቶችን መገንባት፣ማስገንባት፣ማከራየትና መሸጥ ፤በተለየ ሁኔታ ሲወሰን መግዛት፤የፌደራል መንግሥት በባለቤትነት የያዛቸውን ቤቶችና ይዞታዎች ማስተዳደር፣ማከራየት፤ለፌደራል መንግስት ቤቶችና ሕንጻዎች አስፈላጊውን ጥገናና ዕድሳት በማድረግ የመጠበቅና የመንከባከብ ኃላፊነት ተሰጥቶት በመስራት ላይ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም