የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ የእናቶችና የሕጻናት ሞት ከ30 እስከ 40 በመቶ መቀነስ ይቻላል- የጤና ሚኒስቴር

185

ሰኔ 05 ቀን 2014 (ኢዜአ)የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ተደራሽነት የእናቶችና የሕጻናት ሞት ከ30 እስከ 40 በመቶ መቀነስ እንደሚያስችል የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ተደራሽነት የተመለከተ ውይይት ትናንት በድሬዳዋ ከተማ ተካሄዷል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ የቤተሰብን እቅድን አገልግሎት ጥራት ባለው መንገድ ተደራሽ ማድረግ የእናቶችና ሕጻናት ሞትን ከ30 እስከ 40 በመቶ ይቀንሳል ብለዋል።

በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ 3 ነጥብ 1 እስከ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሕጻናት እንደሚወለዱ ገልጸው እነዚህን አዲስ ትውልዶች የሚሸከም ኢኮኖሚ አለመገንባቱን ገልጸዋል።

የተመጠነ የቤተሰብ ቁጥር እንዲኖር በማድረግ የበለጸገች አገር መገንባት አምራች ኃይል መፍጠር እንደሚቻል አመልክተዋል።

በዚህ ረገድም የድሬዳዋ አስተዳደር የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ምጣኔን በ2014 ዓ.ም በጀት ዓመት ከ38 በመቶ ወደ 42 በመቶ ማድረሱ መልካም የሚባል ተሞክሮ እንደሆነ ነው ሚኒስትሩ የገለጹት።

የጤና ባለሙያዎች የአገልግሎቱን ጥራት ለማሳደግ በቁርጠኝነት እንዲሰሩ አሳስበዋል።የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር በበኩላቸው አስተዳደሩ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ የሚያስፈልገውን የፋይናንስ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

የተሻለች ኢትዮጵያ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው ብለዋል።በውይይቱ ላይ በድሬዳዋ አስተዳደር በ2014 ዓ.ም በጀት ዓመት በቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ለተገኘው ውጤት አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት የዋንጫና የምስክር ወረቀት ተበርክቷል።

በየዓመቱ የሚመዘገበው የእናቶች ሞት እየቀነሰ ቢመጣም አሁንም ከ100 ሺህ እናቶች 401 የሚሆኑት በወሊድና ከወሊድ ጋር ተያይዞ ለሕልፈተ-ሕይወት እንደሚዳረጉ የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

ሚኒስቴሩ የሞት ምጣኔውን መቀነስ ያስችላል ያለውን እ.አ.አ በ2030 የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት በአገር አቀፍ ደረጃ ጥራቱን ጠብቆ ተደራሽ እንዲሆን የሚያስችል የቃልኪዳን ሰነድ በታህሳስ ወር 2014 ዓ.ም ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው።

በ2030 ከ18 አመት በታች ያሉ ልጆች እርግዝና አሁን ካለበት 13 በመቶ ወደ 3 በመቶ፣የቤተሰብ እቅድን እየፈለጉ ማግኘት ያልቻሉትን ደግሞ አሁን ካለበት ከ17 በመቶ ወደ 22 በመቶ ለማሳደግ ታቅዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም