ለመኸር ግብርና የሚያስፈልገው የአፈር ማዳበሪያ ግብአት በበቂ መጠን እየቀረበ ነው –ግብርና ሚኒስቴር

4

ባህር ዳር ሰኔ 5/2014 (ኢዜአ) ለዘንድሮው የመኸር ወቅት የሚያስፈልገውን የአፈር ማዳበሪያ ግብአት በበቂ መጠን እንዲቀርብ እየተደረገ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚነስቴሩ የግብዓት አቅርቦትና ስርጭትን በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር በባህር ዳር ከተማ ምክክር አካሂዳል።

በሚኒስቴሩ የግብርና ግብዓትና ገብይት ዳይሬክተር አቶ መንግስቱ ተስፋ እንዳሉት በ2014/15 የምርት ዘመን በቂ የአፈር ማዳበሪያ እየቀረበ ነው።

ቀደም ሲል ከዓልም አቀፍ ወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ለምርት ዘመኑ የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ አስቸጋሪ ሁኔታ አጋጥሞ እንደነበርና በእዚህም ውስን ማዳበሪ እንኳ ማቅረብ አይቻልም የሚል ስጋት እንደነበረ ገልፀዋል።

ይሁን እንጂ መንግስት ባደረገው  ጥረት የገጠሙ ችግሮችን በመቋቋም 60 ቢሊዮን ብር ወጭ በማድረግ 12 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያውን ግዥ መፈፀሙን ገልፀዋል።

ዘንድሮ በግዢ የገባውና ቀድሞ ከነበረው 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል በመጨመር ለምርት ዘመኑ 15 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ እየቀረበ መሆኑን ተናግረዋል።

እስከሁን በተደረገ ጥረት ተገዛው ጂቡቲ ወደብ ከደረሰው 10 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ መካከል 9 ሚሊዮኑ ተጓጉዞ ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱን አስረድተዋል።

እስካሁን  ከ4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ እንዲደረስ መደረጉንም ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

አቶ መንግስቱ እንዳሉት ዘንድሮ ከዓለም አቀፍ ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር የማዳበሪያ ዋጋ በእጅጉ ከፍ ማለቱን ጠቅሰው ፤በዋጋ ጭማሪው ላይ አርሶ አደሩና የግብርና ባለሙያው ቅሬታ ሲያቀርብ መቆየታቸውን ጠቅሰዋል።

መንግስት የአርሶ አደሩን የመክፈል አቅም በማገናዘብ ለመጀመሪያ ጊዜ 15 ቢሊዮን ብር ወይም የዋጋውን 25 በመቶ ድጎማ ማድረጉን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

ይህም ማዳበሪያው የተገዛበት ዋጋ በኩንታል በአማካኝ የ1ሺህ 100 ብር ቅናሽ እንዲኖረው የሚያደርግ መሆኑን አብራርተዋል።

ከዚህ በኋላ የሚፈፀመው የማዳበሪያ ሽያጭ የዋጋ ማስተካከያውን ታሳቢ ባደረገ መንገድ እንደሚሆን አቶ መንግስቱ ተናግረዋል።

ቀደም ሲል ግዥ የፈፀሙ አርሶ አደሮች በትርፍ የከፈሉት ገንዘብ በቀጣይ በሚወርደው አቅጣጫ መሰረት የሚተገበር መሆኑን አስታውቀዋል።

ምርታማነትን ለማሳደግ ሁሉንም ግብዓት በተሟላ መንገድ መጠቀም እንደሚገባ የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ “ዘንድሮ በአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ችግር ምክንያት የሚመጣ የምርት መቀነስ አይኖርም” ነው ያሉት።

‘’ባለፉት ወራት ከውጭ የተገዛውን ማዳበሪያ ችግሮችን ተቋቁሞ በማጓጓዝ በሁሉም ክልሎች እንዲደርስ እየተደረገ ነው’’ ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ምክትል ስራ አስፈፃሚ አቶ ሲራጅ አብድላሂ ናቸው።

የማዳባሪያ ማጓጓዝ ስራው ካለፈው ዓመት በአንድ ወር ዘግይቶ መጀመሩን ጠቁመው፣ በቀን እስከ 230 ተሽከርካሪዎችን በመመደብ የማጓጓዝ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

“እስከሁን በተደረገ እንቅስቃሴም በአጠቃላይ ከተገዛው 12 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ 73 በመቶ ያህሉን በማጓጓዝ ወደሀገር ውስጥ ማስገባት ተችሏል” ነው ያሉት።

ቀሪውን ማዳበሪያ በተቀናጀ አግባብ በፍጥነት በማጓጓዝ ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የግብርና ግብዓትና ገጠር ፋይናንስ ዳይሬክተር ወይዘሮ ሙሽራ ሲሳይ በበኩላቸው፣ የአፈር ማዳበሪያው ባለፉት ጊዜያት ሲቀርብ ከነበረው ጊዜ መዘግየቱን አንስተዋል።

በክልሉ ከ8 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ ታቅዶ እስከሁን 3 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል ወደ ክልሉ መግባቱን ገልጸው 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ለአርሶ አደሩ መድረሱን ተናግረዋል።

“የዋጋ ጭማሬው አርሶ አደሩ የቀረበለትን ማዳበሪያ ፈጥኖ እንዳይወስድ አድርጎታል የሚል እምነት አለኝ”ያሉት ዳሬክተሯ በአሁኑ ወቅት የተደረገው የዋጋ ማስተካከያ የችግሩን የሚቀርፍ ነው ብለዋል።

ማዳበሪያው የዘር ወቅት ከማለፉ በፊት እንዲሰራጭ በየደረጃው የነበሩ ችግሮች በቅንጅት እየተፈቱ መሆኑን ገልፀዋል።

በባህር ዳር ከተማ በተከሄደው የግብርና ግብዓት አቅርቦትና ስርጭት የምክክር ምድረክ የፌደራልና የክልል ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል ።