በድህነት ተኮር የልማት ሴክተሮች የሙስናና ሌብነት ተጋላጭነትን ለመቀነስ እየተሰራ ነው-- ኮሚሽኑ

118

አዳማ ሰኔ 5/2014 (ኢዜአ) ድህነት ተኮር በሆኑ የልማት ሴክተሮች የሙስናና ሌብነት ተጋላጭነትን ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑን የፌዴራል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ የሁሉም ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች የስነ ምግባር መኮንኖች የተሳተፉበት የምክክር መድረክ እያካሄደ ሲሆን  በዓለም ባንክ  የሚደገፉ የልማት  ፕሮጀክቶች ላይ  ሊኖር የሚችለውን ሌብነት ለመከላከል በሚቻልበት ሂደት ላይ እንደሚመክር ተመልክቷል።

በፌዴራል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የስነ ምግባር ግንባታ ዲቪዥን አስተባባሪ አቶ ሀረጎት አብረሀ በዚህ ወቅትእንደገለፁት  ድህነት ተኮር በሆኑ  የልማት ሴክተሮች  የሙስናና  ሌብነት  ተጋላጭነትን  ለመቀነስ እየተሰራ ነው።

በተለይ በዓለም ባንክ በሚደገፉ ግብርና፣ መንገድ፣ ጤና፣ ትምህርትና የውሃ ሴክተሮችን ጨምሮ ሌሎች ተቋማት የሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶችና የሚሰጡ አገልግሎቶችን ከሙስና የፀዱ ለማድረግ  በመስራት ላይ እንደሚገኙ ነው የገለጹት።

በተለይ የሴክተሮቹ አገልግሎትና የግንባታ ፕሮጄክቶች ለሙስና የተጋለጡ በመሆናቸው ከህብረተሰቡ የሚመጡ ጥቆማዎችን  አደራጅተው ለኮሚሽኑ ሪፖርት የሚያደርጉ መኮንኖች  በክልል፣ በዞንና በወረዳ ደረጃ ተደራጅተዋል ብለዋል።

የሙስና ስጋትና ተጋላጭነት ልየታና ጥናት፣ የመረጃ አደረጃጀትና አያያዝ ዙሪያ መኮንኖቹ በቂ ዕውቀትና ክህሎት እንዲኖራቸው መደረጉንም ተናገረዋል።

የፀረ ሙስና ትግሉ ተቋማትን መሰረት ያደረጉ ናቸው ያሉት አስተባባሪው ችግር ያለባቸውን ሴክተሮች በጥናት የመለየት ስራ እየተከናወነ መሆኑንም አመልክተው በፕሮጀክት ላይ የሚፈፀም ሙስናና ሌብነትን ለመከላከልና ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚያስችል ስርዓት እየተዘረጋ  ነው ሲሉ ተናግረዋል ።

ሙስና በድህነት ተኮር የልማት ሴክተሮች ላይ በስፋት የሚስተዋል ቁልፍ ችግር መሆኑን የገለፁት ደግሞ በኮሚሽኑ የዓለም ባንክ የልማት ፕሮጀክቶች አስተባባሪ ታደሰ ደምሴ ናቸው።

በተለይ ትምህርት፣ ጤና፣ መንገድ፣ ውሃናሌሎች ተቋማት ላይ የሚፈፀም ሙስና መከላከል፣ የሙስና ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሚመጡ ጥቆማዎችና  መረጃዎች በአግባቡ ተደራጅተው ለኮሚሽኑ መድረስ እንዳለባቸው ገልጸዋል ።

የክልሎችና የፌዴራል ፀረ ሙስና ሴክተሮች ግንኙነት መላላት ህዝቡ በሙስናና ሌብነት ችግር እንዲማረር በር የሚከፍቱ በመሆናቸው የተቀናጀና የተናበበ  ርብርብ ያስፈልጋል ነው ያሉቱ ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም