ፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ያስተዋወቀበትን የገርጂ መኖሪያ መንደር ግንባታ ፕሮጀክትን አስመረቀ

163

ሰኔ 05 ቀን 2014 (ኢዜአ) ፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ያስተዋወቀበትን የገርጂ መኖሪያ መንደር ግንባታ ፕሮጀክትን አስመረቀ ፡፡

በፕሮጀክቱ "አልሙኒየም ፎርምወርክ ቴክኖሎጂ" የተሰኘ ዘመናዊ የግንባታ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ ያዋለ ሲሆን፤ ኢትዮጵያዊያን ሙያተኞች ቴክኖሎጂውን በማላመድ ግንባታውን በፍጥነት ያከናወኑበት መሆኑም ነው የተጠቆመው፡፡

ቴክኖሎጂው የግንባታ ጥራትና ፍጥነትን የሚያቀላጠፍ እንደሆነም ታውቋል።

ኮርፖሬሽኑ ይህን ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ በማዋልም በገርጂ የመኖሪያ መንደር አስር ወለል ያላቸው 16 ህንጻዎችን በ18 ወራት ጊዜ ውስጥ ገንብቶ ማጠናቀቅ  ችሏል።

የመኖሪያ መንደሩ ዘመናዊ የደህንነት ጥበቃ ስርዓት የተገጠመለት፣ ከ800 በላይ መኪና ማቆም የሚያስችል ስፍራ፣ የጋራ መጠቀሚያ አዳራሽ፣ የተለያዩ ስፖርት መስሪያ ቦታዎች፣ ካፌና ሬስቶራንት፣ መናፈሻ፣ አምፊ ቴዓትር፣ የልጆች መጫወቻንና መዋኛ ገንዳን ያካተተ መሆኑም ተገልጿል።

የገርጂ መኖሪያ መንደር ዘመናዊ የግንባታ ቴክኖሎጂን ማስተዋወቅ ያስቻለ፤ ብቃት ያላቸው የመንግስት ፕሮጀክት መሪዎች የታዩበት፤ አሰሪ፣ የግንባታ አማካሪ እና ተቋራጮች  ለአንድ ዓላማ በትብብር በመስራት ትልቅ ነገር እውን ማድረግ  እንደሚችሉ ያሳየ ነው ተብሏል።

በተጨማሪም የግንባታ ፕሮጀክቱ  ዘመናዊ የግንባታ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የከተሞች የመኖሪያ ቤት እጥረትን መፍታት እንደሚቻል ትምህርት የሰጠ እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም