ሰላም ለሁለንተናዊ እንቅስቃሴ መሰረት በመሆኑ ሁሉም ሊጠብቀው ያስፈልጋል

2

ሶዶ ሰኔ፣ 4/2014 (ኢዜአ) ሰላም ለሁለንተናዊ እንቅስቃሴ መሰረት በመሆኑ የሁሉንም ትኩረት እንደሚሻ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደኣ አስገነዘቡ።

ዛሬ በወላይታ ሶዶ ከተማ “ኢትዮ-ሰላም ሩጫ በወላይታ” በሚል መርህ ቃል የ5 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የሩጫ ውድድር ተካሂዷል።

በኢትዮ-ሰላም ሩጫ ላይ የተሳተፉት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደአ፤ ሰላም ለልማት ለእድገትና ለአብሮነት መሰረት መሆኑን ተናግረዋል።

ለሁለንተናዊ እንቅስቃሴያችን መሠረት የሆነው ሰላም በዘላቂነት እንዲጠበቅ የሁሉንም ዜጋ ትኩረት የሚሻ ነው ብለዋል።

የሀገር ሰላም መጠበቅ ሀገሪቱን ዕድገትና የልማት አማራጮችን በመጠቀም የታለመውን የብልጽግና ግብ ለማሳካት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ የምትታወቅበትን ሩጫ በየአከባቢው ያሉ ዕሴቶችን በማልማትና የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የተጀመሩ ጥረቶች ውጤታማ እንዲሆኑ የሰላም ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።

አቶ ታዬ እንዳሉት ላለፉት ጊዜያት በወላይታና አካባቢው ተፈጥሮ የነበረውን አለመረጋጋት ያስታወሱት ሚኒስትር ዴኤታው አሁን ላይ አካባቢው ወደቀደመ ሰላምና መረጋጋት መመለሱ በግልጽ እንደሚታይ የሚስተዋሉ መልካም የልማት እንቅስቃሴዎች አመላካች ናቸው።

በአከባቢው ዕሴት መሰረት የተፈጠረውን አለመረጋጋት በንግግር ለመፍታት የተደረገው ጥረት ያፈራው ፍሬ መሆኑን እንደሚያመላክት አስታውቀዋል።

እንደ ሀገር በተለያዩ አከባቢ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ተሞክሮ ሊወሰድበት የሚችል መሆኑን አመልክተዋል ።

የወላይታ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አድማሱ አወቀ በበኩላቸው የኢትዮ-ሰላም ሩጫ ለአትሌቲክስ ዘርፍ በአከባቢው የነበረውን  ተሳትፎ  ከፍ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

አስተዳደሩ በቀጣይ ባለው አቅም ለዘርፉ ዝንባሌ ያላቸውን ወጣቶች ለማውጣት በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

ዛሬ የተካሄደው “ኢትዮ-ሰላም ሩጫ በወላይታ” ዓላማው የቀድሞ ዳሞታ አትሌቲክስ ክለብ መልሶ ለማደራጀትን መነቃቃት ለመፍጠር መሆኑን የገለጹት ደግሞ የዞኑ ስፖርትና ወጣቶች መምሪያ የስፖርት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አኮዬ ጌካ ናቸው።

በወላይታና አከባቢ ካለው መልከአ ምድር አቀማመጥ አንጻር ትኩረት ከተሰጠበት በዓለም አደባባይ ሊያስጠሩ የሚችሉ አትሌቶች ማፍለቅ እንደሚቻል ነው የተናገሩት።

በሩጫው ላይ 20 ሺህ የሚሆን ህዝብ የተሳተፈበት ሲሆን በሴቶችና በወንዶች ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃ በመሆን ላጠናቀቁ ከ10 ሺህ እስከ 5 ሺህ ብርና ሽልማት ተበርክቷል።