ዩኒቨርሲቲው በማህበረሰብ አገልግሎት የባህር ዳር ከተማን እያገዘ ነው

4

ባህር ዳር ሰኔ 4/2014 (ኢዜአ) የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለከተማ እድገት በማህበረሰብ አገልግሎት የሚጠበቅበትን ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ የከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሣህሉ ገለጹ።

ዩኒቨርሲቲው 60ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ለማክበር ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገልጿል።

የባህዳር ከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሣህሉ የዩኒቨርሲቲው 60ኛ ዓመት በአልን አስመልክቶ  ለጋዜጠኞች በተሰጠው መግለጫ ላይ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው ለባህር ዳር ከተማ እድገት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ አስተዋጽኦ አድርጓል።

በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በመፍታት መንግስትን እያገዘ ይገኛል ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው የባህዳር ከተማን ለ30 ዓመታት ሊያሰራ የሚችል ስትራክቸራል ፕላን በማዘጋጀት ለእድገቱ ወሳኝ ድርሻ ማበርከቱን ተናግረዋል።

ለባህር ዳር ከተማ ሁለንተናዊ እድገት ወሳኝና ታላቅ አስተዋጽኦ ያበረከተና እያበረከተ ያለ ተቋም በመሆኑ የበለጠ እንዲስፋፋ ከተማ አስተዳደሩ የሚጠበቅበትን እገዛ ያደርጋል ነው ያሉት።

በአዲሱ ዓመት የሚከበረው 60ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በደመቀ ሁኔታ እንዲካሄድ አስተዳደሩ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኘ በበኩላቸው የ60ኛ ዓመት የምስረታ በዓል አከባበር ባለፉት ዓመታት ያስመዘገባቸውን ውጤቶች ለማህበረሰቡ ለማስተዋወቅ ነው።

ለዩኒቨርሲቲው እድገት አስተዋጽኦ የነበራቸውን አካላት በምርምር፣ በኢንቨስትመንትና በሌሎች ዘርፎች በአገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ላገኙ የቀድሞ ምሩቃን እውቅና ለመስጠት ጭምር መሆኑን አስታውቀዋል።

“ከዓባይ ጓዳ ጥበብ ሲቀዳ” በሚል መሪ ቃል የሚታወቀው የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቀደም ሲል ፖሊቴክኒክ ኢንስቲትዩትና ፔዳጎጂ አካዳሚ ይባሉ ከነበሩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጥምረት የተመሰረተ ነው።

ዩኒቨርሲቲው 60ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ከመጪው መስከረም ወር ጀምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበርና  ሰኔ 4/2015 ዓ.ም በልዩ ዝግጅት እንደሚጠናቀቅ አስታውቀዋል።

ዩኒቨርሲቲ በአሁን ወቅት በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች 40 ሽህ የሚጠጉ ተማሪዎችን እያስተማረ እንደሚገኝ ከዩኒቨርሲቲው የተገኘ መረጃ ያስረዳል።