ሁለተኛው የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላት የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ተጠናቀቀ

62

ሰኔ 4/2014/ኢዜአ/ በባሕርዳር ሲካሄድ የቆየው ሁለተኛው የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላት የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ተጠናቀቀ።

በውድድሩ ከሰባት የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላት የተውጣጡ 286 ስፖርተኞች የተሳተፉ ሲሆን ከፍተኛ ፉክክርም አድርገዋል።

በዛሬው እለት ውድድሩ ሲጠናቀቅም ተጠባቂ የነበረውን የወንዶች  5 ሺህ  ሜትር ውድድር ጨምሮ  12  የፍጻሜ ውድድሮች ተካሂደዋል።

በውድድሩ አትሌት ታሪኬ አንተነህ በወንዶች  5 ሺህ ሜትር ቀዳሚ ሆኖ በማጠናቀቅ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ሆኗል።

አትሌት አልዓዛር ተፈራ እና አትሌት አቤል በቀለ እንደ ቅደም ተከተላቸው የብርና የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚዎች ሆነዋል።

በ1 ሺህ 500 ሜትር ደግሞ አትሌት ሳተና ገናሌ፣ አትሌት ታደሰ ሞገስ እና ብዙዓለም ብናልፍ እንደየቅደም ተከተላቸው  ከአንድ እስከ ሦስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።

በሴቶች 3 ሺህ ሜትር የመሰናክል ውድድር አምላክ ፈንታሁን፣  አየሁ ተስፋሁን እና  ደስታ አስፋው  ተከታትለው በመግባት የወርቅ፣ የብርና የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚዎች ሆነዋል ።

በ1 ሺህ 500 ሜትር ደግሞ ምጥን እውነቴ አንደኛ፣  አበበች መሀመድ ሁለተኛ ስትወጣ ሃና ጨምዴ ሦስተኛ ሆና አጠናቃለች።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተሳትፎና ውድድር ዳይሬክተር አስፋው ዳኜ፤ ፌዴሬሽኑ የማሰልጠኛ ማዕከላትን ለማበረታታት በየዓመቱ የስፖርት ትጥቅና የገንዘብ  ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን አስታውሰዋል።

የውድድሩ ዓላማም የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላት  ያሉበትን ደረጃ የሚፈትሹበትና የውድድር እድል እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪ አቅም ያላቸው አትሌቶች ለሌሎች ትላልቅ ውድድሮች ለመሳተፍ እራሳቸውን የሚያሳዩበት  መሆኑንም ተናግረዋል።

በውድድሩ አንዳንድ አትሌቶች ያስመዘገቡት ሰዓት በብሔራዊ ቡድን ከሚመረጡ አትሌቶች ጋር የሚቀራረብ በመሆኑ ጥሩ ውጤት የታየበት ነው ብለዋል።

በባሕርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ለሦስት ቀናት ሲካሄድ በቆየው ውድድር በቆጂ፣ ሀገረሰላም፣ ተንታ፣ ቦሬ፣ ደብረብርሃን፣ ደባርቅና ጂንካ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላት ተሳትፈዋል ።