በዲፕሎማሲው መስክ ጫና ለማሳደር የተሞከሩ ጥረቶችን ኢትዮጵያ እውነታዎችን ይዛ በተጨባጭ ሥራዎች አክሽፋለች

3

ሰኔ 4/2014/ኢዜአ/ በበጀት ዓመቱ በዲፕሎማሲው መስክ ጫና ለማሳደር የተሞከሩ ጥረቶችን ኢትዮጵያ እውነታዎችን ይዛ በተጨባጭ ሥራዎች ማክሸፏን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናገሩ።

ኢትዮጵያ በመጠናቀቅ ላይ ባለው የ2014 በጀት ዓመት በርካታ ፈተናዎችን አሳልፋለች።

በተለይም በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ መንግሥት በወሰደው የሕግ ማስከበር እርምጃ ከውጭ በርከት ያሉ ጫናዎችን አስተናግዷል።

በሌላ በኩል የታላቁ የህዳሴ ግድብ ሁለተኛው የውሃ ሙሌት ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ውሃን ከመጠቀም መብቷ ጋር ተጻራሪ የሆኑ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎች ሲደረጉ መቆየቱም ይታወሳል።

በበጀት ዓመቱ አጠቃላይ በዲፕሎማሲው መስክ የነበሩ ፈተናዎችንና የተመዘገቡ ስኬቶችን በሚመለከት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በነበራቸው ቆይታም የውጭ ኃይሎች መንግሥት ሰላምን ለማስፈን ያደረጋቸውን ጥረቶች ሁሉ ዝቅተኛ ግምት በመስጠት ዲፕሎማሲያዊ ጫና ለመፍጠር የሚሰሩ እንደነበሩ አስታውሰዋል።

ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ የውሃ ሙሌት ዋዜማ ጀምሮ የኢትዮጵያን በሃብቷ የመጠቀም መብት የሚቃወሙ አገራት ሌሎችን በማስከተል ጫና ለማሳደር ብዙ ጥረቶችን ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።

እውነታን ባለመያዝ በተለያዩ ሰበቦች በዲፕሎማሲው መስክ ጫና ለማሳደር የተሞከሩ ጥረቶችን ኢትዮጵያ እውነታዎችን ይዛ በተጨባጭ ሥራዎች ማክሸፏን አምባሳደር ዲና ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አቻ ተቋም በጋራ እንዲያጠኑ መደረጉንና ምክረ-ሃሳቦችም እንዲተገበሩ ግብረ- ኃይል ተቋቁሞ መሰራቱንም ጠቁመዋል።  

ለትግራይ ክልል ሰብዓዊ እርዳታ ፈላጊዎች ያለገደብ እየቀረበ የሚገኘው ድጋፍ ደግሞ ሰብዓዊ እርዳታ እየቀረበ አይደለም የሚሉትን ኃይሎች አጀንዳ ሐሰተኛነት አረጋግጧል ብለዋል።

ስለሰላም የሚነሳውን ጉዳይም መንግሥት ከአፍሪካ እስከ አውሮፓ ድረስ የሚመጡ ልዑካንን ለሰላም ሁሌም ዝግጁ መሆኑን በየጊዜው ገልጾላቸዋል፤  ይህ የመንግሥት አቋም  መንግሥትን ጦረኛ ነው የሚሉ አካላትን ምክንያት የለሽ አድርጓቸዋል ነው ያሉት።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስብሰባዎች  ኢትዮጵያን አጀንዳ አድርጎ የማቅረብና በተጽዕኖ ለማሳደር መሞከር  የተለያዩ ማዕቀቦችንም ለመጣል ሲሞክሩ ነበር ብለዋል።

የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚዳፈሩ ብዙ ሙከራዎች መደረጋቸውንም ጠቅሰው፤ መንግሥትና ኢትዮጵያዊያን በትዕግስትና በጥበብ ጫናውን ለመቋቋም ያደረጉት ጥረት ውጤታማ ነበር ይላሉ።

አምባሳደር ዲና አክለውም በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን  የውጭ ኃይሎች በኢትዮጵያ ላይ የሚያሳርፉትን ጫና በመቃወም ያደረጓቸው ትግሎች የአገሪቱን የዲፕሎማሲ ጉልበት አፈርጥሞታል ብለዋል።

በተለይም ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን  ደግሞ በ”ኖ-ሞር” “በቃ” ዘመቻ በውጭ አገራት ያደረጓቸው እንቅስቃሴዎችም የራሳቸው ውጤት እንደነበራቸው ጠቅሰዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን ለማስከበር የሚፋለም ቆራጥ ሕዝብና አመራር እንዳላት እንዲሁም ዳያስፖራው ከኢትዮጵያዊያን ጋር በችግር ጊዜ ለአገራቸው እንደሚቆሙ በተግባር ያረጋገጠ ዓመት ነበር ብለዋል።

ያም ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያም በዲፕሎማሲው መስክ ጥሩ ትምህርት የወሰደችበት ዓመት እንደነበርም ነው ያነሱት።  

ኢትዮጵያ ፈተና ላይ በነበረችበት ወቅት የቁርጥ ቀን ወዳጅ አገራት ከጎኗ እንደነበሩ ጠቅሰው፤ ለዚህም ኢትዮጵያ ታመሰግናቸዋለች ብለዋል።

የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ባለመገንዘብ የተሳሳተ አቋም ይዘው የነበሩ አገራት ወደ ትክክለኛው መንገድ እንዲመለሱ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቱ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ የምትከተለው የዲፕሎማሲ ዘይቤ ኩርፊያ የሌለበትና በትጋት እውነታውን በማስረዳት ላይ ያተኮረና ውጤት እያስመዘገበ የሚገኝ ነው ብለዋል።

በዚህ ሂደትም በኢትዮጵያ ላይ የተሞከሩ ጫናዎች ሁሉ መክሸፋቸውን ገልጸዋው ኢትዮጵያ አሁንም ዲፕሎማሲያዊ ጥረቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።