የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ተቋማዊ ነጻነት መረጋገጥ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት ያስችላል

127

ሰኔ 4/2014/ኢዜአ/  የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ተቋማዊ ነጻነት ካረጋገጡ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት እንደሚያስችላቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንትና የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የምክክር መድረክ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ገለጹ።

የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የምክክር መድረክ የሁሉም ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶችና የትምህርት ሚኒስቴር  ከፍተኛ ኃላፊዎች በተገኙበት በአዲስ አበባ ተደርጓል።

የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ /ተቋማዊ ነጻነት እንዲያገኙ/ የሚያስችል የአሰራር ሥርዓት ለመዘርጋት በሂደት ላይ መሆኑ በመድረኩ ተገልጿል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ይህንኑ አሰራር በሦስት ወራት ውስጥ ተፈጻሚ ያደርጋል ተብሏል።

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሣሙኤል ክፍሌ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ መንግሥት የዩኒቨርሲቲዎችን ተቋማዊ ነጻነት ለማረጋገጥ እየሰራ ነው።

ይህም ዩኒቨርሲቲዎች ተቋማዊ ተልዕኳቸውን በላቀ ጥራት እንዲፈጽሙ የሚያስችል ነው ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲዎቹ ይህንን አሰራር ተግባራዊ ሲያደርጉ ከመንግሥት በጀትና ድጋፍ ሙሉ በሙሉ ነጻ ይሆናሉ ማለት ሳይሆን ለላቀ ውጤት በጋራ ለመሥራት የሚያስችል ይሆናል ነው ያሉት።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንትና የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የምክክር መድረክ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በበኩላቸው፤ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ተቋማዊ ነጻነት ሳይኖራቸው መቆየቱን ገልጸዋል።

ይህም ዩኒቨርሲቲዎቹ የራሳቸውን ተልዕኮ በራሳቸው መወሰን እንዳይችሉ ማነቆ ሆኖ የቆየ መሆኑን በማንሳት፤ በአሁኑ ወቅት በአገር አቀፍ ደረጃ ተቋማዊ ነጻነት ዘርፈ-ብዙ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።

በዚህም ዩኒቨርሲቲዎች የሚሰጣቸውን ተግባርና ኃላፊነት በብቃትና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ በመወጣት፣ ቴክኖሎጂን ከማስረጽና ኢኮኖሚን ከማሳደግ አኳያ ሰፊ ሚና እንደሚኖራቸው ገልጸዋል።

ያም ሆኖ ራስን የማስተዳደር ተቋማዊ ነጻነት ተጠያቂነት በሰፈነበት መንገድ ሊተገበር የሚገባው እንደሆነም ገልጸዋል።

ይህ አሰራር ተግባራዊ ሲደረግ ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎች በማሰባሰብ በአሰራር ላይ ቅልጥፍናን ማምጣትና ኃብት ለመፍጠር የሚያስችል እንደሆነም አክለዋል።

የተለያየ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች በበኩላቸው፤ አሰራሩ ተግባራዊ ሲደረግ ዩኒቨርሲቲዎቹ አቅማቸውን ተጠቅመው በእውቀት የላቀ ሚናቸውን እንዲወጡና ኃብት ለማመንጨትም ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው ብለዋል።

በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተቋማዊ ነጻነት መረጋገጥ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆን የሚያስችል መሆኑ ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም