የሕግ ማስከበር ተግባራትን በማጠናከር የሽብር ተጋላጭነትን መቀነስ ይገባል

277

ሰኔ 4/2014/ኢዜአ/ በኢትዮጵያ የሕግ ማስከበር ተግባራትን በማጠናከር የሽብር ተጋላጭነትን መቀነስ እንደሚገባ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ።

ሽብርተኝነትን መከላከል ላይ ትኩረት አድርጎ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው አገር አቀፍ የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት ውይይት ዛሬ ተጠናቋል።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል ተመስገን ጥሩነህ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ በውይይት አገራዊ የጸጥታ ሥራና ተግባራት ተገምግሟል።

በውይይቱ ሽብርተኝነት አሁን ያለበት ደረጃ፣ በምሥራቅ አፍሪካ ያለው አክራሪነትና ጽንፈኝነት፣ ፍልሰትና ሌሎች ጉዳዮች ተነስተው ሰፊ ውይይት እንደተካሄደባቸው ተናግረዋል።

ምሥራቅ አፍሪካ ሽብርተኞች እንዲንቀሳቀሱና እንዲያብቡ አመቺ ቀጣና ከመሆኑ አንጻር የመከላከል ሥራ ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።   

የሽብር ቡድኖችን በገንዘብና በሥልጠና የሚደግፉ አካላት መኖራቸው በቀጣናው ሽብርተኝነት እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ ማድረጉንም አብራርተዋል።

ለሽብርተኝነት ከሚያጋልጡ ጉዳዮች አንዱ የውስጥ ክፍተት በመሆኑ በኢትዮጵያ ሁኔታ የሕግ ማስከበር ተግባር አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ አስረድተዋል።

እንደ ዳይሬክተር ጄነራሉ ገለጻ "የሕግ ማስከበር ተግባር በላላ ቁጥር ለሽብርተኞች፣ ለአክራሪዎች፣ ለጽንፈኞችና ወንጀለኞች አመቺ በመሆኑ በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል" ብለዋል።

በተጨማሪም በዞን፣ በክልልና በወረዳ እንዲሁም በክልልና በፌደራል መንግሥት መካከል ፈጣን የመረጃ ልውውጥ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

ወደ አገር ውሰጥ የሚገቡ ስደተኞችን በሚገባ ማጥራት፣ መመዝገብ፣ ማወቅና መከታተልም እንደሚያስፈልግ ዳይሬክተር ጄነራሉ አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን በመዋጋት በምሥራቅ አፍሪካ ያላትን የመሪነት ሚና ማስቀጠል እንደሚገባም አሳስበዋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄነራል አምባሳደር ፍስሃ ሻወል በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገሮች ጋር ሽብርተኝነትን ለመከላከል በትብብር እየሰራች ነው ብለዋል።

የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ተስፋሁን ጎበዛይ፤ ከስደተኞች ጋር ተያይዞ ሊከሰቱ የሚችሉ የሽብር ስጋቶችን ለመከላከል የተጠናከረ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎችን በማጥቃት ዓለም አቀፍ ጫና ለመፍጠር የሚደረጉ ሙከራዎችን ለመከላከልም ከፌደራልና ከክልል የጸጥታ ተቋማት ጋር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሽብርተኝነትን ለመከላከል የጋራ ርብርብ ስለሚፈልግ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት በጋራ በመሥራት አስፈላጊውን ተግባራት ማከናወን እንደሚገባቸው በመድረኩ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም