ትምህርት ቤቶች ለሀገር የሚጠቅሙ ዜጎች መፍለቂያ ለማድረግ የተጠናከረ ስራ መስራት ያስፈልጋል-ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው

148

ሀዋሳ ሰኔ 04/2014 (ኢዜአ) ትምህርት ቤቶች ለሀገር የሚጠቅሙ ዜጎች መፍለቂያ ሆነው ለትውልድ እንዲሻገሩ የተጠናከረ ስራ መስራት እንደሚያስፈልግ ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ዝናሽ ታያቸው አስታወቁ ።

የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን አበሽጌ ወረዳ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ያስገነባው የረገ ኤያት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዛሬ ተመርቋል ፡፡

ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ዝናሽ ታያቸው እንደገለጹት በጽህፈት ቤታቸው እየተከናወነ ያለው የትምህርት ቤቶች ግንባታ ራስንና ቤተሰብን ብሎም ሀገርን መጥቀም የሚችል የተማረ ሰው ማፍራትን ተቀዳሚ ዓላማ አድርጎ ነው ።

ትምህርት ቤቶች ለሀገር የሚጠቅሙ ዜጎች መፍለቂያ ሆነው ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሻገሩ የወላጆች፣ የመምህራንና ባለድርሻ አካላት ጥረት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል ።

ህብረተሰቡ ትምህርት ቤቱን በአግባቡ ተንከባክቦ የሚፈለገውን አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ እንዳለበት ነው ያሳሰቡት።

የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው በበኩላቸው ትምህርት ቤቱ ኢትዮጵያ ከኋላ ቀርነትና ድህነት ተላቃ የብልፅግና ባለቤት እንድትሆን ትምህርት ቁልፍ ሚና አለው ብለዋል።

"ቀዳማዊት እመቤት በመላ ሀገሪቱ ትምህርት ቤቶች እንዲስፋፉ በሚያደርጉት ብርቱ ጥረት ለትውልድ የሚቆይ ደማቅ ታሪክ እያኖሩ ናቸው" ሲሉ ገልጸዋል።

ትምህርት ቤቱ በሥነ ምግባር የታነፁ፣ በዕውቀት የበለፀጉና ሀገር ወዳድ ዜጎችን እንዲያፈራ የሁሉም አካላት ርብርብ እንዳይለይም ጠቁመዋል።

የአካባቢው ነዋሪ አቶ ተማም ኑሩ በአካባቢው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ልጆችን ለማስተማር አስቸጋሪ ሆኖባቸው እንደነበረ ተናግረዋል ።

''ልጆቻችን ነገ የላቀ ደረጃ ይደርሳሉ በሚል ሙሉ ተስፋ ለማስተማር የምንችልበት ተቋም በማግኘታችን እጅግ ተደስቻለሁ'' ብለዋል።

የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት የዘመናት ችግራቸውን የሚያቃልል ትምህርት ቤት ገንብቶልናል ነው ያሉት።

ሌላው የቀበሌ ነዋሪ አቶ ደሳለኝ ወልደደ ቂርቆስ ከዚህ በፊት ልጆቻቸውን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ለማስተማር ወደ አጎራባች ከተሞች ስንቅ በመቋጠር ይልኩ እንደነበር ገልጸው ''ከእንግዲህ እኛም ካልተገባ ወጪ፤ ልጆቻችንም ከእንግልት ይላቀቃሉ'' ብለዋል።

ትምህርት ቤቱን በአግባቡ በመያዝና ለሚያስፈልግ ተጨማሪ ግንባታ የገንዘብም ሆነ የጉልበት አስተዋጽኦ በማድረግ ለቀጣዩ ትውልድ ጠብቆ ለማቆየት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል ።

የስምንተኛ ክፍል ተማሪው ማቱሳላ ሰይፉ ታላላቆቹ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ለማግኘት ሲሉ አቅም ያላቸው በብስክሌት፣ የሌላቸው ደሞ በእግራቸው ረጅም ርቀት ይሄዱ እንደነበር አስታውሷል።

የስምንተኛ ክፍል ትምህርቱን ሲያጠናቅቅ በቀጣይ የሚማርበትን ትምህርት ቤት በአቅራቢያው በማግኘቱ መደሰቱንም ተናግሯል ።

አሁን ላይ በሰነቀው ተስፋ በመበረታታት ትምህርቱን በከፍተኛ ትኩረት እየተከታተለ መሆኑን ተናግሯል።

በምረቃ ሥነ-ሥርዐቱ ላይ ለቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው በጉራጌ ባህል ለሴቶች የክብር ስጦታ የሆነው የወተት ላም ተበርክቶላቸዋል ።

በምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሐመድ ጀማልና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የአካባቢው ማህበረሰብ ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም