የህጻናት ደህንነትን፣ የሴቶችን፣ወጣቶችንና አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሁሉም መስሪያ ቤቶች መስራት ይጠበቅባቸዋል-- ምክር ቤቱ

ሀዋሳ ሰኔ 4/2014 (ኢዜአ) የህጻናት መብትና ደህንነትን ለማስጠበቅ የሴቶችን፣ወጣቶችንና አካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሁሉም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በባለቤትነት መስራት እንዳለባቸው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታወቀ።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ለህዝብ ተወካዮች ምከር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት በተቋሙ ተግባራትና ሃላፊነት ላይ የግንዛቤ መድረከ በሃዋሳ አዘጋጅቷል።

በምክር ቤቱ የጤና ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ወርቅሰሙ  ማሞ  እንዳሉት  በሀገሪቱ  የሴቶች፣ ወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞችና  አረጋዊያን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሊከበሩ ይገባል።

መብቶቹ እንዲከበሩ መንግስት  ጉዳዩን  በባለቤትነት  የሚመራ  ተቋም  በማወቀር  በየደረጃው የተለያዩ ጥረቶች እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በአንድ ተቋም ጥረት ብቻ በተለይ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነታቸውን በተጨባጭ ማረጋገጥ ስለማይቻል ሁሉም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በባለቤትነት መስራት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻቸው እንዲፈቱ እያደረገ ያለውን ጥረት ወይዘሮ ወርቅሰሙ አድንቀዋል።

ተግባሩን በማጠናከር የሴቶች፣ ወጣቶችና  አካል  ጉዳተኞች  ሁለንተናዊ  ተሳታፊነትና  ተጠቃሚነት  ለማጎልበት የህጻናት  መብትና  ደህንነትን  እንዲጠበቅ  ሁሉም አካል በባለቤትነት ሊሰራ እንደሚገባ ነው  የገለጹት።

ሚኒስቴሩ በተሰጡት ተግባራትና ኃላፊነቶች፣ በሚያስፈጽማቸው ፖሊሲዎችና እስትራቴጂዎችን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ላይ ለቋሚ ኮሚቴ  አባላት ያዘጋጀው የግንዛቤ መፍጠሪያ መድረክ ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች እንዳለው አመላክተዋል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ  በበኩላቸው  ሚኒስቴሩ  በየዘርፉ ፖሊሲዎችን፣ስትራቴጂዎችን ፣ፓኬጆችንና የህግ ማእቀፎችን በማዘጋጀት የሴቶችን፣ህጻናትን ፣ወጣቶችን አረጋዊያንና አካል ጉዳተኞችን በላቀ ደረጀ ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ ግብ ይዞ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ ከፌዴራል ጀምሮ በየደረጃው መዋቅሮችን በመዘርጋትና የማስፈጸሚያ ስልቶችን በመንደፍ በበጀት ዓመቱ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት መስራቱን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

ሚኒስቴሩ ለቋሚ  ኮሚቴ  አባላቱ  በአዲሱ  የመንግስት  አስፈጻሚ  አካላት  አደረጃጀት  ስልጣንና ተግባራትን ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1263/2014 እና በሚኒስቴሩ ተግባራትና  ኃላፊነቶች፣  በሚያስፈጽማቸው  ፖሊሲዎችና እስትራቴጂዎችን ጨምሮ  በዓለም  አቀፍ  ስምምነቶች ዙሪያ  ያዘጋጀው  የግንዛቤ  መፍጠሪያ  ስራ  ለሁለት  ቀናት  የሚቆይ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም