በቀበሌ ቤት ሕጋዊ ነዋሪዎች መሆናችን እየታወቀ የወረዳው አስተዳደር አስወጥቶን ለሌሎች ሰዎች ሰጠብን–ቅሬታ አቅራቢዎች

3

ሰኔ 4/2014/ኢዜአ/ በቀበሌ ቤት ሕጋዊ ነዋሪዎች መሆናችን እየታወቀ የወረዳው አስተዳደር አስወጥቶን ለሌሎች ሰዎች ሰጠብን ሲሉ ቅሬታ አቅራቢዎች ተናገሩ።

በአዲስ አበባ አራዳ ክፍለ ከተማ የወረዳ 04 የቤቶች አስተዳደር ጽሕፈት ቤት በበኩሉ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ቤት ደርሷቸው በሌላ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች መሆናቸው በመረጋገጡ የቀበሌው ቤት አይገባቸውም ብሏል።

በክፍለ ከተማው ወረዳ 04 በቀበሌ የቤት ቁጥር 803 ነዋሪ ሆነን ሳለ ወረዳው ከሕግ አግባብ ውጭ አስወጥቶ ሌላ ተከራይ በማስገባት ለችግር ዳርጎናል ሲሉ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ለኢዜአ ተናግረዋል።

የቅሬታ አቅራቢዎቹ በህጉ መሰረት የቤቱ ወራሽ ነን፣ ለእኛ ይገባናል፣ በሃይል ተገደን ወጥተን ልንባረር አይገባም በማለት የሚመለከተው አካል ችግራችንን ተረድቶ መፍትሄ ይስጠን ሲሉ ይጠይቃሉ።

የቀበሌ ቤቱ በወይዘሮ መቅደስ አበበ ስም ተመዝግቦ የሚገኝ ሲሆን እርሳቸው ደግሞ ጥር 14 ቀን 2012 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት በመለየታቸው የቤቱ ስም ወደ እነ አማኑኤል መላኩ በ02/03/2013 ዓ.ም ተዛውሯል የሚል መከራከሪያም ያቀርባሉ።

የእነ አማኑኤል መላኩ ተወካይ የሆኑት አቶ ወርቁ ዘገየ፤ የቤቱ ህጋዊ ወራሾች እያሉ ከህግ አግባብ ውጭ እንዲወጡ መደረጉ ፍፁም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ይገልፃሉ።

የቤቱን ሕጋዊ ነዋሪዎች በግፍ በማስወጣት ለሌላ አካል ማስተላለፉ የወራሽነትን መብት የተጋፋ ነው በማለት የወረዳውን ድርጊት ይቃወማሉ።

የወረዳ 04 የቤቶች አስተዳደር እኛ ሳናውቅ የምንኖርበትን የቀበሌ ቤት ለሌላ ግለሰብ ከማስተላለፉም በላይ የቤት እቃዎቻችንን ጭኖ ወስዶብናል ሲሉም ቅሬታቸውን አቅርበዋል።

በቤቱ ላይ የፍርድ ቤት እግድ ያወጣን ቢሆንም የወረዳ 04 የቤቶች አስተዳደር ህጉን ባለማክበር ለሌላ ግለሰብ ከማስተላለፉም በላይ የቤት እቃዎቻችንን ጭኖ ወስዶብናል ብለዋል።

በዚሁ ጉዳይ ሌላኛዋ ቅሬታ አቅራቢ ወይዘሮ ሶፋኒት ተስፋዬ፤ በህገ ወጥ መልኩ ከቤቱ በማስወጣት ለሌላ አካል በማስተላለፉ በእጅጉ ማዘናቸውን ገልጸዋል።

በአራዳ ክፍለ ከተማ የወረዳ 04 የቤቶች አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሰለሞን ግርማ፤ በጉዳዩ ላይ በሰጡት ምላሽ “ቅሬታ አቅራቢዎቹ በመኖሪያ ቤቱ ላይ ሕጋዊ መብት የላቸውም” ሲሉ ተናግረዋል።

 በወረዳ 04 የቤት ቁጥር 803 ላይ ቅሬታ ያቀረቡት አቶ አማኑኤል መላኩ፤ የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤት  ዕጣ የደረሳቸውና ውጭ አገር የሚኖሩ መሆናቸውን መረጃ አለን ብለዋል።

ወይዘሮ እየሩሳሌም መላኩ ደግሞ በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 የቤት ቁጥር 541 ነዋሪ በመሆናቸው ቤቱን መውረስ አይችሉም ሲሉ አስረድተዋል።

በቤቱ ይኖሩ የነበሩት ወይዘሮ መቅደስ አበበ በሞት ከተለዩ በኋላ አሁንም ውጭ አገር የሚኖረው ልጃቸው አቶ አማኑኤል መላኩ በ2013 ዓ.ም ቤቱን የወራሽነት መብቱን በፍርድ ቤት አሳውጆ ወደ ራሱ ስም ማዛወሩን ገልጸዋል።

ወረዳው ጉዳዩን ለማጣራት በምክትል ሥራ አስፈጻሚ የሚመራ ኮሚቴ አቋቁሞ ሲሰራ መቆየቱን ጠቁመዋል።

በዚህም መሰረት የማጥራት ሥራ ሲሰራ ወራሽ ነኝ ያሉት ወይዘሮ ኢየሩሳሌም መላኩ የልደታ ክፍለ ከተማ ነዋሪ መሆናቸው ተረጋግጧል ብለዋል።

በመሆኑም እርሳቸው በልደታ ክፍለ ከተማ ነዋሪ እያሉ በአራዳ ክፍለ ከተማ የመንግሥት ቤት ወራሽ ነኝ ማለት አይችሉም ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ አቶ አማኑኤል መላኩ የወራሽነታቸውን መብት ያረጋገጡት በ02/03/2013 ሲሆን ወይዘሮ እየሩሳሌም መላኩ ወራሽ ነኝ ብለው የመጡት ግን ከአንድ ወር በኋላ በ09/04/2013 ለወረዳው ቤቶች ሲያመለክቱ ቤቱ እንደማይመለከታቸው በወቅቱ መገለጹን ተናግረዋል።

መኖሪያ ቤቱን በሚመለከት በሸገር ማስዋብ ፕሮጀክት ለተነሱት ሌላ ተከራይ መሰጠቱን አቶ ሰለሞን ገልጸዋል።

የመንግሥት ቤት በአዋጅ ቁጥር 47/67 የተወረሱ እና በመመሪያ ቁጥር 5/2011 የሚተዳደር ሲሆን የቤት ኪራይ ውል ሕጋዊ ተከራይ ባል ከነበረ፤ ባል በህይወት ከሌለ ወራሽ ሚስት ወይም ደግሞ ሁለቱም ከሌሉ ወደ ልጆች የሚተላለፍ መሆኑን በአዋጁ ተመልክቷል።