አሸባሪው ህወሃት ሰብዓዊ እርዳታ በመከልከል እንደጦር መሳሪያ የመጠቀም የቆየ ልምዱን አሁንም እንደቀጠለበት ነው

144

ሰኔ 4/2014/ኢዜአ/ አሸባሪው ህወሃት ሰብዓዊ እርዳታ በመከልከል እንደጦር መሳሪያ የመጠቀም የቆየ ልምዱን አሁንም እንደቀጠለበት አሜሪካዊው የፖለቲካ ተንታኝ አንድሬው ኮሪብኮ ገለጹ።

አሸባሪው ህወሃት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በ1977 ዓ.ም በተከሰተው ድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ከተላከው የ100 ሚሊዮን ዶላር ርዳታ 95 በመቶውን ለጦር መሳሪያ ግዥ እንዳዋለው አይዘነጋም።

ቡድኑ ቀድሞም ቢሆን ይፈፅማቸው የነበሩ እኩይ ተግባራትን የሚያውቁ ተንታኞች አሁንም ለትግራይ ክልል ህዝብ የሚላከውን ርዳታ ለራሱ ጥቅም እያዋለው መሆኑን እያጋለጡ ነው።

አሜሪካዊው የፖለቲካ ተንታኝ አንድሬው ኮሪብኮ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ “ህወሃት ሰብዓዊ እርዳታን ለጦር መሳሪያነት የመጠቀም የቆየ ልማዱን አሁንም ቀጥሎበታል” ብለዋል።

ቡድኑ ለህዝብ ከተላከ የሰብዓዊ ድጋፍ ውስጥ አብዛኛውን በቀጣይ ሊፈፅም ላቀዳቸው ጥቃቶች እያደረገ ላለው የጦር ዝግጅት እያዋለው መሆኑን በማንሳት።

ህወሃት ከውጭ ደጋፊዎቹና አንዳንድ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ጋር እጅ ለእጅ በመያያዝ የቡድኑን ነውረኛነት ለመሸፈን እየሰሩ ነው ብለዋል ኮሪብኮ።

“መንግስት የትግራይ ክልል ህዝብ ተገቢውን ድጋፍ እንዲያገኝ የቻለውን ሁሉ አድርጓል፤ አሁንም እያደረገ ነው፤ ሆኖም የመንግስት ጥረት በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ተገቢውን ትኩረት አላገኘም” ብለዋል።

ህወሃትና ቅጥረኞቹ መንግስት እያደረገ ያለውን ሰብዓዊ ድጋፍ እንዳልተፈጸመ በማንሳት እውነታውን ለመሸፈንና በመንግስት ላይ ጫና እንዲደርስ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህም ባሻገር ህወሃት በቀጣይ ሊፈጽም ላሰባቸው ጥቃቶች አመቺነት በሰብዓዊ እርዳታ ስም ኮሪደሮች እንዲከፈቱ በተደጋጋሚ እየጠየቁ መሆኑን ገልጸዋል።

አሸባሪው ህወሃት የሰብዓዊ ርዳታዎችን በተሳለጠ ሁኔታ እንዳይደርሱ ከማስተጓጎሉም ባሻገር እርዳታውን ከህዝብ ይልቅ ለታጣቂዎቹ እያከፋፈለ ነው ብለዋል።

ሆኖም ህወሃትና የውጭ መገናኛ ብዙሃን እውነታውን በማዛባትና አጀንዳ በማስቀየስ ዓለም አቀፉ ማህብረሰብ አሁንም  በመንግስት ላይ ጫና እንዲያሳድር እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።

የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅቶች ለጦርነት እየተዘጋጀ ለሚገኘው አሸባሪው ህወሃት በሚስጥር እያደረጉ ካለው  የድጋፍ እንቅሰቃሴያቸው እንዲቆጠቡም ጠይቀዋል።

መንግስትም የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች የሀገሪቱን  ህግ አክብረው እንዲሰሩ ተገቢውን ቁጥጥር እንዲያደርግና እርምጃ እንዲወስድ ነው ያስገነዘቡት።

የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬተሪ ቢልለኔ ስዩም ባሳለፍነው ሳምንት በሰጡት መግለጫ ህወሃት በመጪው የእርሻ ወቅት ጦርነት ለመክፈት እየተዘጋጀ መሆኑን መግለፃቸው ይታወሳል።

በትግራይ ክልል ድጋፍ የሚሹ ወገኖች በአሸባሪው እየተወሰደባቸው ሰብአዊ ድጋፍ እየደረሳቸው አለመሆኑን ጠቅሰው ከዚህም በላይ ቡድኑ ህዝቡን በማስገደድ ለጦርነት እየመለመለ መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም