በምዕራብ ወለጋ ዞን በ4ኛ ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ294 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ ችግኞች ይተከላሉ

124

ግምቢ ሰኔ 4/2014 (ኢዜአ) በምዕራብ ወለጋ ዞን በ4ኛ ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚተከሉ ከ294 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች መዘጋጀታቸውን የዞኑ ግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

ለተከላ ከተዘጋጁት ከ294 ሚሊያን ችግኞች መካከል ከ14 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ለምግብነት የሚውሉ መሆኑን ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል።

በጽህፈት ቤቱ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ቡድን መሪ አቶ ፍቅሩ ብርሃኑ እንደገለፁት በዞኑ በ4ኛ ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚተከሉ ከ294 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ ችግኞች ተዘጋጅተዋል።

ችግኞቹ ለእንስሳት መኖ፣ ለሰው ምግብና ለደን ሽፋን የሚያገለግሉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ለችግኞቹ ተከላ 77 ሺህ 426 ሄክታር መሬት መዘጋጀቱንና  ከ59 ሚሊዮን በላይ የችግኝ መትከያ ጓድጓድ መቆፈራቸውንም ገልጸዋል፡፡

የሆማ ወረዳ አርሶ አደር ልጃለም ታሲሳ በየዓመቱ የተለያዩ ችግኞችና ፍሬያቸው የሚበላ አቮካዶ፣ ብርቱካን፣ማንጎና የመሳሰሉት በብዛት በመትክል ከምግብነት አልፎ የተራቆቱ መሬቶችን በመልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በዘንድሮው የተከላ መርሃ ግብር ለምግብነት የሚያገለግሉ ከ1ሺህ በላይ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሌላው ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ዳንኤል ጉርሜሳ  የተፈጥሮ ሀብት መንከባከብ የሁሉም ግዴታ መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

አርሶ አደሩ ከ500 በላይ ለምግብነት የሚያገለግሉ የፍራፍሬ ችግኞችን ለመትከል ጉድጓድ እያዘጋጁ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በየዓመቱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች በግልና በቡድን እንደሚተክሉ የተናገሩት ደግሞ የላሎ አሳቢ ወረዳ አርሶ አደር ዮሴፍ ክፍሉ ናቸው ፡፡

የተለያዩ ጠቀሜታ የሚሰጡ ችግኞች ተክሎ ለማልማት ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የግምቢ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር አምባራስ እምሩ እንደተናገሩት ለምግብነት የሚውሉ ችግኞችን መትከል በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ በመሆኑ ትኩረት አድርገው እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በዘንድሮ ክረምት ለሚያደርጉት ተከላ ችግኞችን በግላቸው ማዘጋጀታቸውን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም