ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በሀገራዊ የምክክር መድረኩ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅበታል - ኢዜአ አማርኛ
ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በሀገራዊ የምክክር መድረኩ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅበታል

ሶዶ ሰኔ 3/2014 (ኢዜአ) ለሀገራዊ የምክክሩ ስኬት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የሚጠበቅበትን ሊወጣ እንደሚገባ የሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ።
"አካታች ብሄራዊ ምክክር ለዘላቂ ሰላማችን፣ ለአብሮነታችንና ለብሄራዊ መግባባታችን" በሚል መሪ ሀሳብ ሀገር አቀፍ የፓናል ውይይት በወላይታ ሶዶ ከተማ ተካሂዷል።
የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ እንደገለጹት ሀገራዊ ምክክሩ በህዝቦች መካከል የሚስተዋሉ አለመግባባቶችን በውይይት በማጥበብ ወደ ህብረ-ብሔራዊ ወንድማማችነት የሚያደርስ መድረክ ነው።
ለሚካሄደው ሀገራዊ ምክክር ስኬታማነት የምሁራን፣ የፖለቲካ ልሂቃን እና የኅብረተሰቡ ርብርብ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
አገራዊ ምክክር ለቀጣይ ሀገራዊ እድገትና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የሚፈለገውን ግብ እንዲያሳካ የዜጎች ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ህብረተሰቡ የምክክሩን ዓላማ በሚገባ በመረዳት ሂደቱን እንዲደግፍም ነው ሚኒስትር ዴኤታው የጠየቁት።
የደቡብ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፋጤ ሰርሞሎ በበኩላቸው በህዝቦች ውስጥ ለሀገራዊ ምክክር መድረኩ መሳካት የሚያግዙ እሴቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።
ሁሉም ህብረተሰብ ያሉትን የሰላም እሴቶች ለሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ሊጠቀምባቸው ይገባል ብለዋል።
የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰ እንዳሉት የአገሪቱ ቀጣይ የሰላምና አብሮነት መጎልበት አገራዊ ምክክርን ስኬታማ በማድረግ ከሁሉም ዜጎች እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።
የሀገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራን፣ ፖለቲከኞችን ጨምሮ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል መዘጋጀት እንዳለበት ጠቁመዋል።
"የምክክር መድረኩ ለኢትዮጵያውያን በርካታ ችግሮች መፍትሔ አምጪ በመሆኑ ግቡን እንዲመታ የበኩላችንን እንወጣ" ሲሉ ተናግረዋል።