መንግሥት በተለያዩ ክልሎች እያከናወነ ያለው ሕግ የማስከበር ተግባር ሰላምን በማስፈን ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል

116

ሰኔ 3/2014/ኢዜአ/ መንግሥት በተለያዩ ክልሎች እያከናወነ ያለው ሕግ የማስከበር ተግባር ሰላምን በማስፈን ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ፡፡

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት መግለጫ ሕዝብን በማወክ ተግባራት ላይ ተሳትፎ የነበራቸው አካላትን በመለየት ሕግ የማስከበር ተግባራት ሲካሄድ ቆይቷል ብለዋል።

ሕግ የማስከበር ሥራውን የሚመራው የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤትም እስካሁን የተከናወኑ ሥራዎች ጥሩ ውጤት እንደተመዘገበባቸው መገምገሙን ተናግረዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በሸኔ የሽብር ቡድን ላይ በተወሰደው እርምጃ የሽብር ቡድኑ ሲንቀሳቀስባቸው በነበሩ አካባቢዎች አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ በአማራ ክልል እየተወሰደ ባለው የሕግ ማስከበር እርምጃ ሰላምና መረጋጋትን ማስፈን መቻሉን ጠቅሰው፤ ከዚሁ ሥራ ጎን ለጎንም የማኅበረሰቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ ውይይት እየተደረገ ነው ብለዋል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም በተለያዩ ወንጀሎች ተሳታፊ የነበሩ ግለሰቦችን በተለይም በኮንትሮባንድ እና በሽብር ተግባራት ሲሳተፉ የነበሩ አካላትን በቁጥጥር ሥር ማዋል መቻሉን ገልጸዋል፡፡

በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ሆነው በሙስና እና ሕገ-ወጥ ተግባራት የተሰማሩ አካላት ላይም ሕግ የማስከበር ሥራ መከናወኑን ጠቅሰው፤ ይህ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

መንግሥት የዜጎችን ሰላም ለማስጠበቅ የሚያከናውነውን ሕግ የማስከበር እርምጃ ይበልጥ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም እንዲሁ፡፡

መንግሥት እያከናወነ ያለው ሕግ የማስከበር እርምጃ ውጤታማ እንዲሆን እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ነው ሚኒስትር ዴኤታዋ ጥሪ ያቀረቡት፡፡

የሰብዓዊ ድጋፍን በተመለከተም በአማራ ክልል በሰሜን ወሎና ዋግ ኽምራ ዞን፣ በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን እና በአፋር ክልል ሦስት ዞኖች በችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች  ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በትግራይ ክልልም መንግሥት ከዓለም አቀፍ እርዳታ ተቋማት ጋር በመተባበር ሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ እንዲሆን እየተደረገ ስለመሆኑ አብራርተዋል፡፡

በተለይ የዓለም አቀፍ ተቋማት እያደረጉት ያለው ድጋፍ በቂ አለመሆኑን ገልጸው፤ ተቋማቱ የሚያቀርቡትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በማህበራዊና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በሰጡት ማብራሪያም ከመጋቢት 21 ቀን 2014 እስከ ግንቦት መጨረሻ ድረስ  በሳዑዲ አረቢያ በችግር ውስጥ የነበሩ ከ35 ሺህ በላይ  ዜጎችን ወደ ኢትዮጵያ መመለስ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም