የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መፅሐፍት አገልግሎት ለአብርሆት የ3 ሚሊዮን ብር መፅሐፍት አበረከተ

4

ሰኔ 3/2014/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መፅሐፍት አገልግሎት ለአብርሆት ቤተ መጽሃፍት የ3 ሚሊዮን ብር የተለያዩ መፅሐፍት አበረከተ።

ለአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት “ሚሊዮን መጻሕፍት ለሚሊኒየሙ ትውልድ በሚል መሪ ኃሳብ” እየተከናወነ ላለው መጻሕፍት የማሰባሰብ ንቅናቄ የተለያዩ ተቋማት ምላሽ እየሰጡ ይገኛሉ።

ለዚሁ መርሃ ግብር በዛሬው እለት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመፅሐፍት አገልግሎት የ3 ሚሊዮን ብር መፅሐፍት አበርክቷል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመፅሐፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ይኩኖአምላክ መዝገቡ፤መጽሃፍቱን በአብርሆት ቤተ መጽሃፍት በመገኘት አስረክበዋል።

የተበረከቱት መፅሀፍት በኢትዮጵያውያን የተፃፉ የታሪክ፣ የልብወለድና ሌሎች ይዘቶችንም ያካተቱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳው፤ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመፅሐፍት አገልግሎት ላበረከታቸው መጻሕፍት ምስጋና አቅርበዋል።

በቀጣይም ከመጽሀፍት ድጋፍ ባለፈ ሙያዊ እገዛ ጭምር እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ አራት ኪሎ አካባቢ ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው አብርሆት ሁለገብ ቤተ-መጽሐፍት 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን መጽሐፍትን የመያዝ አቅም እንዳለው ይታወቃል።