የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ ክትባቱን እንዲወስድ ለህብረተሰቡ ጥሪ ቀረበ

6

ሐዋሳ ሰኔ 3/2014 (ኢዜአ) የኮቪድ -19 ወረርሽኝ ዳግም ቢከሰት የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል እንዲቻል እድሜያቸው 12 ዓመትና ከዛ በላይ የሆኑ በዘመቻ እየተሰጠ ያለውን የመከላከያ ክትባት እንዲወስዱ የጤና ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ።

የሲዳማ ክልል 3ኛው ዙር የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ማስጀመሪያ ፕሮግራም  በሀዋሳ  ተካሂዷል።

በመርሃ ግብሩላይ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ለኢዜአ እንደገለጹት 3ኛው ዙር የኮቪድ-19  ክትባት  በሁሉም ክልሎች በዘመቻ እየተሰጠ  ይገኛል።

ባለፉት ሁለት ዙሮች በተካሄደው የክትባት ዘመቻ በርካታ ውጤቶች መገኘታቸውን ገልጸው በተለይ በ2ኛው ዙር  በርካታ ሰዎች ክትባቱን መውሰዳቸውን አመላክተዋል።

በየደረጃው በሚገኙ ጤና ተቋማትና በተለያዩ ቦታዎች በተደረገው የክትባት መርሃ ግብር 24 ነጥብ 5 ሚሊዮን ህዝብ ቢያንስ አንድ ጊዜ ክትባት መውሰዱን ገልጸው ይህም እድሜያቸው 12 እና ከዛ  በላይ ከሚሆነው ህዝብ መካከል 44 በመቶ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይህንን በማጠናከር የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ዳግም በሀገሪቱ እንዳያገረሽና ችግር ቢከሰት እንኳን ብዙ ሰዎች ለከፋጉዳትእንዳይዳረጉ ማህበረሰቡ ክትባቱን በነቂስ ወጥቶ እንዲወስድ ጥሪ አቅርበዋል።

ከክትባቱ ጋር ተያይዞ  ተገቢ ያልሆነና ከእውነት የራቁ ውዥንበር እንደሚነዛ የገለጹት ዶክተር ደረጀ ይህንን ለማጥራት ሚኒስቴሩና በየደረጃው የሚገኙ የጤና ሴክተሮች ትክክለኛ መረጃ እየሰጡ ናቸው።

በመሆኑም በ3ኛው ዙር እድሜው  12 ዓመት የሞላ ሁሉ መከተብ እንዳለበት ጠቅሰው በተለይ ከዚህ በፊት አንድ ዶዝ ወስደው ድጋሜ መውሰድ ያለባቸው ከ6 ወር በላይ የቆዩ የማጠናከሪያ ክትባት እንዲወስዱ አስገንዝበዋል።

በከተማ አካባቢ የግንዛቤ እጥረት በመኖሩ ክትባቱን የመውስድ ምጣኔው ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አውሰተዋል።

ዶክተር ዱጉማ  አሁን ላይ በበሽታየሚያዘው ሰው ቁጥር ከፍ እያለ መምጣቱንና በተለይ አዲስ አበባ ላይ በየቀኑ ብዙ ሰዎች ኮቪድ እየተገኘባቸው ይገኛል ብለዋል።

በፅኑ ህሙማን ክፍል ተኝተው የሚታከሙም ህሙማን በመኖራቸው እንደ ሀዋሳ ያሉ ትላልቅ ከተሞች ላይ ወረርሽኙ ሊከሰት ስለሚችል ማህበረሰቡ  ክትባቱን መውሰድ እንዳለበት አሳስበዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ በ3ኛው ዙር 25 ሚሊዮን ሰዎችን ለመከተብ የተያዘው እቅድ እንዲሳካ ሁሉም በባለቤትነት እንዲሳተፍ መልእክት አስተላልፈዋል።    

የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሠላማዊት መንገሻ በበኩላቸው በሲዳማ ክልል ከሚገኘው ህዝብ መካከል 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን የሚሆነው ክትባቱን መውሰድ ይጠበቅበታል ብለዋል።

ዕድሜያቸው 12 ዓመትና ከዚያ በላይ የሚሆናቸው ፣ ከዚህ በፊት ክትባት ያልወሰዱ፣ አንድ ጊዜ ወስደው ሁለተኛውን ያልወሰዱ እንዲሁም ሁለተኛውን ከወሰዱ 6 ወር የሞላቸው  የመከላከል አቅም የሚጨምረውን ሶስተኛ “ዶዝ” እንዲወስዱ ጥሪ አቅርበዋል።

በክልሉ በሚገኙ በሁሉም ወረዳዎችና ከተሞች በመደበኛና ጊዜያዊ የክትባት መስጫ ጣቢያዎች በመገኘት ህብረተሰቡ በሁለተኛ ዙር ዘመቻ በታየው መነሳሳትና በተገኘው ውጤት ልክ  እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።