አሸባሪው ሕወሓት ሰብዓዊ ድጋፍን ከሕዝብ በመንጠቅ ለጦርነት የማዋሉን ተግባር አሁን የጀመረው ሳይሆን በታሪክም የሚታወቅበት ነው

97

ሰኔ 3/2014/ኢዜአ/ አሸባሪው ሕወሓት ሰብዓዊ ድጋፍን ከሕዝብ በመንጠቅ ለጦርነት የማዋሉን ተግባር አሁን የጀመረው ሳይሆን በታሪክም የሚታወቅበት መሆኑን የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ከፍተኛ ኃላፊዎች ገለጹ፡፡

የፓርቲው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እንደሚሉት፤ ለትግራይ ክልል ሕዝብ አስከፊ ችግር ውስጥ መግባት ዋናው ተጠያቂ  አሸባሪው ሕወሓት ነው።

አሸባሪው ሕወሓት ከትጥቅ ትግል ጀምሮ ለሕዝቡ ሳይሆን ለራሱ ህልውና ሲታገል የቆየ ድርጅት መሆኑን ጠቅሰው፤ ቡድኑ ለሕዝብ የሚላክን ሰብዓዊ ድጋፍ በመቀማት ለጦርነት የማዋል ልምድ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ምክትል ሊቀመንበር መስፍን ደሳለኝ፤ አሸባሪው ሕወሓት በ1977 ዓ.ም ለትግራይ ሕዝብ የተላከን ድጋፍ ቀምቶ ለትጥቅ ትግል ማዋሉን አስታውሰዋል፡፡

ይህ ደግሞ በድርጅቱ መስራቾችና መሪዎች መካከል ልዩነት እንዲፈጠር በማድረግ የተወሰኑት ድርጅቱን እንዲለቁ ያስገደደ ክስተት እንደነበር ነው የተናገሩት፡፡

አሸባሪ ቡድኑ አሁንም ወደ ትግራይ ክልል የሚላከውን ድጋፍ ለታጣቂዎቹ እያዋለ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተመሳሳይ የፓርቲው የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ሐጎስ ግደይ፤ ቡድኑ ወደ ትግራይ እየተላከ ያለውን ሰብዓዊ ድጋፍ  ለጦርነት የሚያሰልፋቸውን ታጣቂዎች ለመመልመል እየተጠቀመበት መሆኑን ያብራራሉ፡፡

በዚህም ሰብዓዊ ድጋፉን በዋናነት ለታጣቂዎቹና ታጣቂ ቤተሰቦች እያከፋፈለ መሆኑን ጠቅሰው፤ አብዛኛው የትግራይ ሕዝብ በችግር ላይ መሆኑን አውስተዋል፡፡

በትግራይ ክልል ልጁን ለጦርነት ያልሰጠ ቤተሰብ እርዳታ እንደማያገኝም ነው የገለጹት፡፡

በዚህም የሽብር ቡድኑ ከራሱ ውጭ ለትግራይ ሕዝብ እንደማያስብ በተግባር አረጋግጧል ነው ያሉት፡፡

የሽብር ቡድኑ በፍጹም የሚለወጥ የፖለቲካ ድርጅት አለመሆኑን ያነሱት አቶ መስፍን፤ የትግራይ ሕዝብ ከገጠመው ችግር ለመውጣት ''አሸባሪው ሕወሓትን አምርረን ልንታገለው ይገባል'' ብለዋል፡፡

አቶ ሐጎስ ግደይ በበኩላቸው፤ የትግራይ ሕዝብ ልጆቹን ለጦርነት መስጠት እንደማይፈልግ በግልጽ የሽብር ቡድኑን እየተቃወመ መሆኑን ገልጸው፤ ይህንኑ ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በውጭ አገር የሚኖሩ የትግራይ ክልል ተወላጆች አሁን ላይ የቡድኑ አካሄድ ስህተት መሆኑን በመገንዘብ እየተቃወሙት እንደሚገኙም አንስተዋል።

በአሥር ወራት ውስጥ 87 ሺህ ሜትሪክ ቶን ምግብ-ነክ ድጋፍ ወደ ትግራይ ክልል እንደተላከ የኢትዮጵያ መንግሥት መግለጹ ይታወቃል።

በተጨማሪም መድኃኒትን ጨምሮ ምግብ-ነክ ያልሆኑ ድጋፎች፣ ነዳጅና ሰብዓዊ ድጋፉን ለማቀላጠፍ የሚውል ጥሬ ገንዘብ ወደ ክልሉ መላኩም እንዲሁ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም