በኢንዱስትሪና ዩኒቨርሲቲዎች መካከል በጋራ የመሥራት ጉዳይ ወጥነት ባለው መልኩ እየተተገበረ አይደለም

106

ሰኔ3/2014/ኢዜአ/ በኢንዱስትሪና ዩኒቨርሲቲዎች መካከል ለአገር ልማት በጋራ የመሥራት ጉዳይ ወጥነት ባለው መልኩ እየተተገበረ አለመሆኑን አንድ ጥናት አመለከተ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢንዱስትሪና ዩኒቨርሲቲዎች መካከል የቴክኖሎጂ ሽግግር በማስረጽ በጋራ መሥራት የሚያስችል የዳሰሳ ጥናት ይፋ አድርጓል።

በጋራ ለመሥራት የሚያስችል ሁኔታዎች ቢፈጠሩም ወጥነት ባለው መልኩ እየተተገበረ አለመሆኑ በጥናቱ ተመልክቷል።

በዚህም የዩኒቨርሲቲዎች ጥናትና ምርምር ጥቅም ላይ ያለመዋልና ለኢንዱስትሪዎች የሃሳብ ግብአት እየሆነ አይደለም ተብሏል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ምትኬ ሞላ፤ የሁለቱ ሴክተሮች ተመጋጋቢነት ለማኅበረሰብ ተጠቃሚነትና ለአገር እድገት ወሳኝ በመሆኑ ሊሰራበት ይገባል ብለዋል።

ለዚህም ስኬት በተደረገው ጥናት መሰረት በሁለቱም ተቋማት በኩል በጋራ መሥራት የሚያስችል ወጥነት ያለው የአሰራር ሥርዓት መዘርጋት ይገባል ነው ያሉት።

በዩኒቨርሲቲው የዘርፉ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ዳንኤል ጣሰው፤ ኢትዮጵያ ወደ ኢንዱስትሪ መርነት የምታደርገውን ጥረት እውን ለማድረግ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል።

የበለጸጉት  አገራት ዩኒቨርሲቲዎችና ኢንዱስትሪዎቻቸው በጋራ በመሥራት የላቀ ስኬት ማስመዝገባቸውን ጠቅሰው፤ ለኢትዮጵያም ጥሩ ተሞክሮ መሆን አለበት ነው ያሉት።

በዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ሙያ ማበልጸጊያ ዳይሬክተር ዶክተር ካሱ ጂልቻ በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲዎች ለአገር ልማትና እድገት ከሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ባለፈ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን መሥራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ያሉ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ከኢንዱስትሪዎች ጋር በጥምረት የሚሰሩበትን መንገድ ለመፍጠር ዝግጁ ሊሆኑ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም