ምሁራን ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በመስራት ለሀገር ለውጥ የሚጠበቅባቸውን ሊወጡ ይገባል – ሚኒስቴሩ

8

ሚዛን አማን፣ ሰኔ 03/2014 (ኢዜአ) የዩኒቨርስቲ ምሁራን ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ውጤቶችን በማውጣት ለሀገር ሁለንተናዊ ለውጥ የሚጠቅሙ የመፍትሄ ሀሳቦችን ማቅረብ እንደሚገባቸው የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ ።

የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ 11ኛው ሀገር አቀፍ የጥናትና ምርምር ጉባኤ ዛሬ መካሄድ ጀምሯል።

በኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር የምርምርና ማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ሰሎሞን ቢኖር እንዳሉት ምሁራን ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምሮችን በመስራት የዜግነት ግዴታቸውን መወጣት አለባቸው።

የምርምር ሥራዎች የህብረተሰቡን ችግር መፍታት የማይችሉ ከሆነ ትርጉም የላቸውም ያሉት ዶክተር ሰሎሞን ምርምሮች  በጥንቃቄና በጥራት መሰራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር አህመድ ሙስጠፋ በበኩላቸው ውጤታማ ጥናትና ምርምሮች ለሀገር እድገትና ለውጥ ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።

ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ፈጠራ ለእድገት መሠረት ናቸው ያሉት ፕሬዝዳንቱ ለህብረተሰባችን የተሻለ የአኗኗር ዘይቤ ለመፍጠር ምሁራን ተሞክሮ እየተለዋወጡ ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

“ዩኒቨርሲቲዎች ያላቸውን እምቅ አቅም ለሀገራዊ የጋራ ተጠቃሚነት እንዲያውሉ ጠይቀው በተለይ የማኅበረሰቡን እሴቶች ማልማትና አገልግሎት እንዲሰጡ ማስቻል ያስፈልጋል” ብለዋል።

የዩኒቨርስቲው ምርምርና ማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር አብዮት አስረስ በጉባኤው ለሀገራዊ ዕድገት መሰናክሎች መፍትሄዎችን የሚያመላክቱ  የጥናትና ምርምር ውጤቶች ይቀርባሉ።

ዩኒቨርስቲው በሚገኝበት አካባቢ ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሀብትና የማኅበረሰብ ባህልና እሴቶች ላይ ትኩረት ያደረጉ ጥናቶችንም እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

የዘንድሮ 11ኛ ጥናትና ምርምር ጉባኤ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ፈጠራ ለሀገራዊ ዕድገት ያላቸው ሚና ላይ ትኩረት በማድረግ መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።

በዩኒቨርስቲው ቴፒ ካምፓስ ለሁለት ቀናት በሚቆየው ብሔራዊ የምርምር ጉባኤ 61 ጥናታዊ ጽሑፎች ይቀርባሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን 21 ዩኒቨርሲቲዎችና 3 የምርምር ተቋማት እየተሳተፉ ይገኛሉ።