በሰሜን ሸዋ ዞን 223 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ወደ ግንባታ ገብተዋል

54

ደብረብርሀን ሰኔ 3/2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን 13 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 223 ፕሮጀክቶች የግንባታ ስራ መጀመራቸውን የዞኑ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ አስታወቀ፡፡

የዞኑ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ ሉባባ መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት አካባቢው ለልማት ካለው ምቹነት አንፃር የኢንቨስትመንት ቀጠና እየሆነ መጥቷል።

በዞኑ በርካታ ባለሃብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ለመሰማራት ፈቃድ ወስደው በተለያየ የግንባታ ሂደት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በተለያየ ጊዜ ፈቃድ ወስደው ከ13 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 223 የኢቨስትመንት ፕሮጀክቶች ከመንግስት በተሰጣቸው 931 ነጥብ 2 ሄክታር መሬት በግንባታ ላይ ናቸው ብለዋል።

ፕሮጀክቶቹ በኢንዱስትሪ፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በሆቴል ቱሪዝምና ኮንስትራክሽንን ጨምሮ በሌሎች ዘርፎች የሚሰማሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የግንባታ ስራቸው በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ተጠናቅቆ ወደ ማምረት እንደሚሸጋገሩ የገለጹት ሃላፊው በፕሮጀክቶቹ የግንባታ ሂደት ለ23 ሺህ 970 ሰዎች የስራ እድል ተጠቃሚ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ለኢንቨስትመንት የተቀበሉትን ቦታ ለረጅም ጊዜ አጥረው ያስቀመጡ የ25 ፕሮጀክቶች ፈቃድ መሰረዙንና 47 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ መደረጉን ጠቅሰዋል።

አሁን ላይ ባለሀብቶች የሚያነሱትን የኤሌትሪክ ሃይልና ሌሎች የመልካም አስተዳደር ተግዳሮቶች ለመፍታት ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

‘’ጀር ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ አቶ በእውቀቱ ሙሉ በበኩላቸው ከመንግስት በወሰዱት 14 ሄክታር መሬት 11 ኢንዱስትሪዎችን ለመትከል የግንባታ ስራ ጀምረዋል።

ለኢንቨስትመንት በወሰዱት መሬት ላይ ለነበሩት አርሶ አደሮች 20 ሚሊየን ብር የመሬት ካሳ መክፈላቸውን ተናግረዋል።

ከዚህም ሌላ የኢሌክትሪክ ወጪን በመጋራት ከ100 ሚሊየን ብር በላይ ክፍያ መፈጸማቸውን ገልጸዋል።

በዞኑ ቀደም ሲል ግንባታ አጠናቀው በማምረትና አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ 379 ኢንዱስትሪዎች  እንደሚገኙ የመምሪያው መረጃ ያመላክታል።