በፓርኮች የዱር እንስሳት በሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት ለአደጋ እየተጋለጡ መሆኑን የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ገለጸ

311

ሰኔ3/2014/ኢዜአ/ በፓርኮች የዱር እንስሳት በሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት ለአደጋ እየተጋለጡ በመሆኑ ከመጥፋት ለመታደግ የባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ጥረት እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ጠየቀ።

የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን የስርዓተ ምህዳር ክትትልና ምርምር ዳይሬክተር ዶክተር ፈለቀ ረጋሳ የችግሩን አሳሳቢነት በተለመከተ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በገለፃቸውም ብሔራዊ ፓርኮች ላይ የሚፈጸሙ ሰው ሰራሽ አደጋዎች የዱር እንስሳትን ለከፋ አደጋ እየዳረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

በፓርኮች ዙሪያ የእርሻ መስፋፋት፣ የደን ምንጣሮ፣ ልቅ ግጦሽ፣ ሰደድ እሳት፣ ሕገ ወጥ አደንና መሰል ሰው ሰራሽ ተግባራት እየተባባሱ በመምጣታቸው ለዱር አንሰሳቱ መመናመን አይነተኛ ምክንያቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በቅርቡ በተከሰተው በአላይደጌ አሰቦ ዕጩ ብሄራዊ ፓርክ ቀደም ብሎ በሰሜን ተራሮችና በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርኮች ላይ የተከሰቱ ሰደድ እሳቶች በርካታ ዱር እንስሳት መሞታቸውን ገልጸዋል።።

በ2014 ዓ.ም በተደረገ ጥናት በፓርኮች ውስጥ የሚገኙ የዱር እንስሳት ቁጥር እየተመናመነ መጥቷል ብለዋል።

በሰንቀሌ ላይ የሚገኘው ኮርኬ ቁጥሩ አነስተኛ ቢሆንም አሁን ላይ እየጨመረ ወደ 800 መጠጋቱን ተናግረው በባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ እስከ 300 ዝሆኖች እንደገሚኙም አብራርተዋል፡፡

በፓርኮች ውስጥም ሆነ ከፓርኮች ውጭ በሚፈጸም ሕገ ወጥ አደን ሳቢያ ዝሆን፣ አቦሸማኔና አናብስትን ጨምሮ በርካታ ትልልቅ አዱር አጥቢ እንስሳት ጥርስና ቆዳቸውን በሚፈልጉ አካላት እንደሚገደሉ ተናግረዋል።

በዚህም ሳቢያ እስከ መጥፋት የሚደርስ አደጋ የተደቀነባቸው የዱር እንስሳት መኖራቸውን ነው ያብራሩት፡፡

ከብርቅዬ እንስሳት መካከል አንዱ ቀይ ቀበሮ በፓርኮች ውስጥ በሚለቀቁ ዕብድ ውሾች በሽታ የሚጋለጡበት አጋጣሚ እየተስፋፋ መሆኑን ገልጸው አሁን ላይ የቀይ ቀበሮዎች ቁጥር አሽቆልቁሎ 500 መድረሱን ገልጸዋል።

በአውሮፓዊያኑ 2015 ቁጥሩ 900 የነበረው ዋሊያ በ2021 ወደ 700 ማሽቆልቆሉን ጠቅሰው በባሌ ብሔራዊ ፓርክ የሚገኙ የደጋ አጋዘኖች ቁጥር 1 ሺህ 300 ገዳማ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

የዱር እንስሳት መመናመን እና የብሔራዊ ፓርኮች አደጋ ተጋላጭነት ለመቀነስ ባለስልጣኑ ህብረተሰብ አቀፍ ስራዎችን እያከናወነ ስለመሆኑ  አንስተዋል።

የሰደድ እሳትን ከመቆጣጠር ጀምሮ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን የህብረተሰቡን ግንዛቤ የማሳደግ ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

የዱር እንስሳቱን ለመጠበቅ ክልሎችም ሆኑ በቅርበት የሚገኙት ወረዳዎች ጭምር የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ በኩል የድርሻቸውን እንዲወጡ ዶክተር ፈለቀ ጥሪ አቅርበዋል፡፡   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም