የሽብርተኝነት አደጋን ለመከላከል ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ትብብርን ወደ ላቀ ደረጃ የማሳደግ ተግባር በመከናወን ላይ ነው

95

ሰኔ 03 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የሽብርተኝነት አደጋን ለመከላከል ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ትብብርን ወደ ላቀ ደረጃ የማሳደግ ተግባር በመከናወን ላይ መሆኑን የብሔራዊ መረጃና ደሕንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

"ሽብርተኝነትን በመከላከል የጋራ ቤታችን የሆነችውን ኢትዮጵያ በጋራ እንጠብቃለን!" በሚል መሪ ሃሳብ አገር አቀፍ የጸጥታና ደህንነት ተቋማት ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል ተመስገን ጥሩነህ፤ ሽብርተኝነት አገርና ሕዝብን አደጋ ላይ የሚጥል ዓለም አቀፍ ስጋት በመሆኑ የመከላከል ተግባሩ ሁሉንም ይመለከታል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ላይ ሊቃጡ የነበሩ የሽብር ድርጊቶችን በማክሸፍና በመከላከል ሂደት የተሳካ ስራ መሰራቱንም አስታውሰዋል።

May be an image of 2 people and people standing

በዚህ ተግባር አጠቃላይ የሕዝቡና የጎረቤት አገሮች አቻ ተቋማት የነበራቸውን ሚና አድንቀው ቀጣይነት እንዲኖረውም ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያ የሽብርተኝነት አደጋን ለመከላከል ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ትብብሯን ወደ ላቀ ደረጃ የማሸጋገር ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆኗንም ጠቅሰዋል።

ሽብርተኝነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ስጋት ሆኖ የቀጠለ የጋራ ችግር በመሆኑ የጋራ መከላከልን ይጠይቃል ብለዋል።

በውይይት መድረኩ ወቅታዊ የሽብርተኝነት ስጋቶችና የመፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ ሰፊ ውይይት እንደሚደረግ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም