ዩኒቨርሲቲው ከጸሃይ ብርሃን የኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰጥ ቴክኖሎጂ በማበልጸግ በጉራጌ ዞን ለሚገኘው ሰራራ ትምህርት ቤት አበረከተ

7

ሰኔ 3/2014/ኢዜአ/ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከጸሃይ ብርሃን የኤሌክትሪክ ኃይል መስጠት የሚችል ቴክኖሎጂ በማበልጸግ በጉራጌ ዞን ለሚገኘው ሰራራ ትምህርት ቤት አበረከተ፡፡

ቴክኖሎጂው በዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ በዚነስ ማላመጃ ማዕከል የበለጸገ ሲሆን፤ ላለፉት ሦስት ዓመታት ምርምር ሲደረግበት ቆይቷል።

በዚህም የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ከቤታቸው በቻርጅ የሚሰራ አምፖል/መብራት /በማምጣትና በማእከሉ  ቻርጅ በማድረግ የኤሌክትሪክ ብርሃን የሚያገኙ ይሆናል፡፡

በተጨማሪም እስከ አንድ ሺህ ስልኮችን ቻርጅ ማድረግ የሚችል እንደሆነም ነው የተገለጸው።

ተማሪ ሀሰን ሸሪፍ በሲራራ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን በሚኖርበት አካባቢ የኤሌክትሪ ኃይል ባለመኖሩ ምክንያት በምሽት ለማንበብም ሆነ የቤት ስራ ለመስራት ሲቸገር መቆየቱን ይገልጻል።

በምሽት ለማንበብ ኩራዝ ይጠቀም እንደነበር የሚናገረው ተማሪ ሃሰን፤ ይህም ቤተሰቦቹን ለተጨማሪ ወጪ ሲዳርግ መቆየቱን ነው የተናገረው፡፡

ከዚህ አኳያ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በጸሃይ ኃይል የሚሰራ የኤሌክትሪክ ኃይል መስጫ ጣቢያ በትምህርት ቤቱ በመትከሉ ትልቅ እፎይታ አግኝተናል ነው ያለው።   

“አሁን ላይ የኤሌክትሪክ ሃይል መስጫ አምፖሎችን ከጣቢያው ቻርጅ በማድረግ በቤታችን ብርሃን እያገኘን ነው፤ ይህም ትምህርታችንን በአግባቡ እንድናጠና አድርጎናል” ሲል ተናግሯል፡፡    

የትምህርት ቤቱ ወላጅ ተወካይ አቶ ትዕግስቱ በዙ በበኩላቸው አገር ተረካቢ ትውልድ ለማፍራት ትምህርት ወሳኝ ሚና እንዳለው ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ የተደረገልን ድጋፍ ልጆቻችን ትልቅ ደረጃ እንደሚደርሱ ተስፋ እንድንሰንቅ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡

የቴክኖሎጂው የፈጠራ ባለቤትና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኤሌክትሪክ ምህንድስና መምህር የሆኑት ኢንጂነር ጌታቸው ተሾመ ፤ጣቢያው እስከ 400 የሚደርሱ ተማሪዎችን የኃይል ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪ እስከ አንድ ሺህ ሞባይል ስልኮችንም ቻርጅ ማድረግ እንደሚያስችል ጠቅሰው፤ይህም ከተማሪዎች ባለፈ ለአካባቢው ማህበረሰብ አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢንጂነር ጌታቸው እንደሚሉት፤የህብረተሰቡን ችግር የሚያቃልሉ ችግር ፈቺ የቴክኖሎጂ ውጤቶች እንዲስፋፉ የፈጠራ ሀሳብ ያላቸውን ባለሙያዎች በትኩረት መደገፍ ይገባል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ችግር ፈቺ የፈጠራ ሀሳቦች ወደ ማበልጸጊያ ማዕከል እየገቡ ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆኑ እየሰራ መሆኑን የተናገረው ደግሞ በዩኒቨርሲቲው ምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ምትኬ ሞላ ናቸው፡፡  

በሰራራ ትምህርት ቤት የየተከለው የኃይል መስጫ ጣቢያ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ መሆኑን ገልጸው፤ መሰል የፈጠራ ስራዎች በሌሎች ትምህርት ቤቶች እንዲስፋፉ ይሰራል ብለዋል፡፡

ቴክኖሎጂው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግርን ከመፍታት ባለፈ ተማሪዎች ለፈጠራ ስራ እንዲነሳሱ አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረውም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡