“የታችኛው ተፋሰስ አገራት በቂ የውሃ ሀብት እያላቸው ኢትዮጵያ የተትረፈረፈ የውሃ ሀብት እንዳላት የሚያነሱት የክርክር ሀሳብ ከእውነት የራቀ ነው”- ዶክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ

78

ሰኔ 03 ቀን 2014 (ኢዜአ) የታችኛው ተፋሰስ አገራት በቂ የውሃ ሀብት እያላቸው ኢትዮጵያ ብቻ የተትረፈረፈ የውሃ ሀብት እንዳላት የሚያነሱት የክርክር ሀሳብ ከእውነት የራቀ ነው ሲሉ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ ገለጹ።

“ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን ለማልማት የማንም አገር ይሁንታ አያስፈልጋትም” ብለዋል።የኢትዮጵያ የውሃ፣ የውሃ ዲፕሎማሲና ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መማክርት ፎረም ትናንት በአርባ ምንጭ ተመስርቷል።

ፎረሙ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና መገናኛ ብዙሃንን ያካተተ ነው። “የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ የሚወሰነው በዜጎቿ፣በመሬቷና በሀብቷ ነው፤ ከዚህ አኳያ የውሃ ሀብቶቿን ለመጠቀም የሌላ አገር ቡራኬ አያስፈልጋትም” ብለዋል ሚኒስትሩ በፎረሙ ላይ ባደረጉት ንግግር።

“የታችኛው ተፋሰስ አገራት በቂ የውሃ ሀብት አላቸው፤ ነገር ግን ኢትዮጵያ የተትረፈረፈ የውሃ ሀብት እንዳላት ይከራከራሉ ይሄ ከእውነት የራቀ ነው” ሲሉ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ “የውሃ ማማ” የተባለችው በ”መልክዐ ምድራዊ አቀማመጥ እንጂ የተትረፈረፈ ውሃ ስላላት አይደለም ” ያሉት ሚኒስትሩ የተፋሰሱ አገራት ስላላቸው የውሃ ሀብት ማውራት አይፈልጉም ብለዋል።

በሌላ በኩል ከውሃ ሀብት አስተዳደርና አጠቃቀም ጋር ተያይዞ የዘርፉ ምሁራንና መገናኛ ብዙሃንን አስተሳስረን መጠቀም ባለመቻላችን የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ የኢትዮጵያን ሀቅና እውነታን እየተረዳ አለመሆኑን አመልክተዋል።

አዲሱ ትውልድ ስለ ውሃ ሀብቶቻችን ግንዛቤ ኖሮት እንዲያድግ በትምህርት ስርዓቱ መታገዝ እንዳለባቸውና ለዚህም መገናኛ ብዙሃን በተለያየ የተግባቦት አማራጮች በመጠቀም የማስተማር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዳምጠው ዳርዛ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከድንበር ተሻጋሪ ወንዞቿ በሚፈለገው መጠን ሳትጠቀም ለዘመናት ቆይታለች ብለዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን ለልማት ለመጠቀም ለጀመረችው ስራ ትልቁ ማሳያ የሚወሰድ ነው ብለዋል።ሁሉም ኢትዮጵያዊ የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅበት አመልክተዋል።

የመማክርት ፎረም መመስረቱ ስለ ኢትዮጵያ ውሃ ሀብቶች በዓለም አቀፍ መድረክ በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሰረ ሙግት ያስችላል ያሉት ደግሞ የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ ናቸው።

ከድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ጋር ያሉ አለመግባባቶችን በውይይት በመፍታት ከቀጠናው አገራት ጋር ያለውን ትብብር ለማጠናከር የሚከናወኑ ስራዎችን መደገፍ እንደሚችል አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ የውሃ፣የውሃ ዲፕሎማሲና ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መማክርት ፎረም በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሀቆች የማስረዳት፣በውሃ ሀብት አስተዳደር ጉዳዮች ሙያዊ ድጋፍ መስጠት፣ዘርፉን የሚያሳድጉ ሳይንሳዊ ምክረ ሀሳቦችን ማቅረብና የስራቸውን ውጤቶች በመገናኛ ብዙሃን የማሰራጨት ተግባር እንደሚያከናውኑ በምስረታው ወቅት ተገልጿል።