ፍርድ ቤቱ መርማሪ ፖሊስ በኮንስታብል አንቡላ ኡቴ ላይ የጠየቀውን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቀደ

134

ሰኔ 3 ቀን 2014 (ኢዜአ) የፌደራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በአዲስ አበባ በኢድ በዓል ላይ ከፈነዳው የአስለቃሽ ጭስ ጋር ተያይዞ ተጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር የዋለው ኮንስታብል አንቡላ ኡቴ ላይ ፖሊስ የጠየቀውን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቀደ።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል መከላከል አድማ ብተና አባል  የነበረው ኮንስታብል አንቡላ ኡቴ  በፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 2ኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርቧል።

በዚሁ ወቅትም ጉዳዩን የያዙት መርማሪ ፖሊሶች እስካሁን ሲያካሂዱ የቆዩትን የምርመራ ውጤት ሪፖርት ለፍርድ ቤቱ አቅርበዋል።

ፖሊስ ከዚህ በፊት በተፈቀደለት የምርመራ ጊዜ የሁለት ምስክሮችን ቃል ተቀብሎ የአንድ ምስክር ቃል የሚቀረው መሆኑን አስታውቋል።

በተጨማሪም  ከብሔራዊ መረጃና ደሕንነት የቴክኒክ ምርመራ ምላሽ እየተጠበቀ  በመሆኑ ውጤቱን ለመጠባበቅና ቀሪ የምርመራ ሥራ ለማከናወን ተጨማሪ 14 ቀናት ያስፈልገኛል ብሏል።
 

በተለይ ''ከብሔራዊ መረጃና ደሕንነት የሚጠበቀው መረጃ ምን አልባትም የፖሊስ የምርመራ አቅጣጫን ሊያስቀይረው ይችላል የሚል እሳቤ እንዳለ'' አንስቷል።

ተጠርጣሪው ከሌሎች አካላት የገንዘብ ድጋፍ ይኑረው አይኑረው ለማጣራት ለግልና ለመንግሥት ባንኮች ለተጻፈው ደብዳቤ  ምላሽም እንዲሁ እየተጠባበቀ መሆኑን በመጠቆም።

የተጠርጣሪው ሌሎች ግብረ-አበሮች እስካሁን በቁጥጥር ሥር ባለመዋላቸው እነርሱን ለመከታተል ተጨማሪ የምርመራ ቀናት እንደሚያስፈልገው ነው የጠቆመው።

የወንጀሉ ተጠርጣሪ ኮንስታብል አንቡላ ኡቴ፤ በካምፕ ውስጥ ነዋሪ መሆኑን እና  በግል ንብረቱ ላይ ብርበራ ተደርጎ የተገኘ ማስረጃ እንደሌለ ተናግሯል።

''እኔ ሕዝብና አገርን የማገለግል ነኝ፤ ምንም  ወንጀል አልሰራሁም፤ የዋስትና መብት ተፈቅዶልኝ ጉዳዬን በውጭ ሆኜ ልከታተል ''ሲልም ጠይቋል።

መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ ተጠርጣሪው ሰዎችን ሊያስፈራራ ይችላል የዋስትና መብት ሊፈቀድለት አይገባም ሲል ተከራክሯል።

ፍርድ ቤቱ የፖሊስን የምርመራ መዝገብ አስቀርቦ በመመልከት ፖሊስ በተሰጠው ጊዜ ማስረጃ የማሰባሰቡን ሥራ በተገቢው መንገድ ማከናወኑን ተረድቻለሁ ብሏል።

በመሆኑም ፍርድ ቤቱ ፖሊስ ከጠየቀው 14 ተጨማሪ ቀናት አሥሩን በመፍቀድ ለሰኔ 13 ቀን 2014 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም