የዋልያዎቹ ተጋድሎ የሀገር ከፍታ ማሳያ

132

ሰኔ 3 ቀን 2014 (ኢዜአ) የዓባይ ልጆች ድል በሁሉም መስክ መመዝገብ እንደሚችል በአንድ ልብና በአንድ መንፈስ በግብጽ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ላይ ድልን የተቀዳጁት ዋልዎቹ ማሳያ ናቸው።

በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኘውን ዋልያ ስያሜ ይዘው በልበ ሙሉነት ወደ እግር ኳስ ሜዳ የገቡት የአባይ ልጆች ሰንደቃቸውን እንደ ዋልያ ከፍ ባለው የአፍሪካዊነት ተራራ ላይ አውለብልበዋል።

ኢትዮጵያ የብዙ ሀገራት የነጻነት ምልክት መሆኗ ታሪካዊ ሃቅ ነው፣ የነጻነት ምልክትነቱ ለሀገራት መመስረት፣ለአፍሪካ ሕብረት መቋቋምና ለፓን አፍሪካኒዝም እውን መሆን መንገድን ያቀናም ነው።

አፍሪካውያን መምራት፣መከላከል፣መዋጋትና ማሸነፍ እንደሚችሉም የኢትዮጵያውን ድል የሆነው አድዋ መነቃቃትን ፈጥሮ ለነጻነት አነሳስቷል።

በስነ እና በኪነ ህንጻ፣ በሃይማኖት ቀደምትነት፣በፊደል ቀረጻ፣ በሀገር በቀል የህዝብ አስተዳደር፣በህክምና በንግድና በመሳሰሉት የሰው ልጅ ስልጣኔ አሻራ በሆኑ ተግባራት ኢትዮጵያ ለአፍሪካ በኩር ሆና በምልክትነት ትታያለች።

ዛሬም ይህን ብኩርናዋን የሚጠብቁ የአፍሪካን ቀንዲል ይዛ ከፊት እንድትመራቸው የሚፈልጉ ልጆቿና ወዳጆቿን አስተባብራ መጓዝ ይኖርባታል።

ለዚህም ሁሉም በየመስኩ እንደ ዋልያዎቹ ለሀገሩና አፍሪካ ከፍታ የሚያደርገው ተጋድሎ ወሳኝ ነው።

ሁሉም በየድርሻውና በየተሰማራበት የሚጠበቅበትን ሲወጣ ኢትዮጵያ ብልጽግናዋን እያረጋገጠች ትቀጥላለች።