በአዲሱ የበጀት ዓመት 10 ሺህ ኩንታል የአቮካዶ ምርት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ዝግጅት እየተደረገ ነው

3

አዳማ ሰኔ 3/2014 (ኢዜአ) በአዲሱ የበጀት ዓመት 10 ሺህ ኩንታል የአቮካዶ ምርት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ገለፀ።

በቢሮው የቡና፣ፍራፍሬና የቅመማ ቅመም ዘርፍ ምክትል ሃላፊ አቶ ሙሐመድ አሚን ለኢዜአ እንደገለፁት በክልሉ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ የአቮካዶ ልማት በ6 ሺህ 100 ሄክታር መሬት ላይ እየለማ ይገኛል።

በ2013/2014 ዓም የምርት ዘመን 200 ኩንታል የአቮካዶ ምርት ወደ እስፔን፣ዩናይትድ አረብ ኤመሬትና ሌሎች ሀገራት መላኩን ገልጸው የምርቱ ተፈላጊነትና ጥራት ከፍተኛ መሆኑን ከተቀባይ ሀገራት ግብረ መልስ መገኘቱን ጠቅሰዋል።

ምርቱን ወደ አውሮፓ፣ መካከለኛው ምስራቅና የኤዥያ ሀገራት ምርቱን ለመላክ መታቀዱን አመላክተዋል።

በአዲሱ በጀት ዓመት 10 ሺህ ኩንታል የአቮካዶ ምርትን ለውጭ ገበያ ለመላክ  በተደረገው ዝግጅት አርሶ አደሩንና ላኪ ድርጅቶችን በማገናኘት የምርት ዋጋ ተመን መቆረጡን ተናግረዋል።

አርሶ አደሮቹ ምርቱን በጥራት በማምረትና በጥንቃቄ  ለድርጅቶቹ እንዲያስረክቡ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተያዘው ክረምት ከ4 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ የአቮካዶ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት መጠናቀቁንም ገልጸዋል።

አቶ ሙሐመድ ዘንድሮ በክልሉ በኤክስፖርት አቮካዶ የሚሸፈን መሬት 10ሺህ ሔክታር ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው በልማቱ 30 ሺህ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ መሆኑን ተናግረዋል።

የምስራቅ ሸዋ ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት ምክትል ሃላፊ አቶ አብነት አሸብር በበኩላቸው በዞኑ 88ሺህ የኤክስፖርት አቮካዶ ችግኝ ለመትከል መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል ።

በአሁኑ ወቅት በዞኑ ስድስት ወረዳዎች በ6 መቶ ሄክታር መሬት ላይ የአቮካዶ ልማት እየተከናወነ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በዘርፉ ልማት ከተሰማሩት አርሶ አደሮች መካከል የሉሜ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ተስፋዬ በዳዳ  25  የአቮካዶ ችግኝ በመትከል ወደ ዘርፉ ልማት መቀላቀላቸውን ገልጸው በአሁኑ ወቅት በ2 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ እያለሙ መሆኑን ተናግረዋል።

አርሶ አደሩ በአንድ ጊዜ የምርት ሽያጭ 97 ሺህ ብር ገቢ ማግኘታቸውን ነው የገለጹት።

ባለፈው አመት አንድ ኪሎ አቮካዶ በ40 ብር መሸጣቸውንና አሁን ባለው ዋጋ 60 ብር  እንደሚያወጣ ተናግረዋል ።