ተቋርጦ የነበረው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሰኔ 7 ይጀመራል

7

ሰኔ 03 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ተቋርጦ የነበረው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም ይጀመራል።

ብሔራዊ ቡድኑ እ.አ.አ በ2023 በኮትዲቭዋር አስተናጋጅነት በሚካሄደው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ለሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ሲባል ፕሪሚየር ሊጉ ከግንቦት 16 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ተቋርጦ ነበር።

ፕሪሚየር ሊጉ ከብሔራዊ ቡድኑ ጨዋታ መልስ በኋላ ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም በ26ኛ ሳምንት መርሃ-ግብሮች እንደሚጀመር የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር አስታውቋል።

ከ26ኛ እስከ 30ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በባህርዳር ይካሄዳሉ። ፕሪሚየር ሊጉ ሰኔ 27 ቀን 2014 ዓ.ም ይጠናቀቃል።

የመጨረሻ ሁለት ሳምንት ጨዋታዎች የቡድኖችን ውጤት መሰረት በማድረግ የቀንና ሰዓት ለውጥ ሊደረግ እንደሚችል ማህበሩ ገልጿል።

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የደረጃ ሰንጠረዥ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ54 ነጥብ እየመራ ነው። ፋሲል ከነማ በ49 ሲዳማ ቡና በ40 ነጥብ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

አዲስ አበባ ከተማ፣ጅማ አባ ጅፋር እና ሰበታ ከተማ ከ14ኛ እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።

የፕሪሚየር ሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን የወልቂጤ ከተማው ጌታነህ ከበደና የሲዳማ ቡናው ይገዙ ቦጋለ በተመሳሳይ 13 ግቦች ይመራሉ።

ጋናዊው የአዲስ አበባ ከተማ ተጫዋች ሪችሞንዶ አዶንጎ በ12 እንዲሁም የኢትዮጵያ ቡናው አቡበከር ናስር በ11 ግቦች ይከተላሉ።