በቋንቋና ስነ-ጽሑፍ መስክ ውጤታማ የሆነው የኢትዮ-ሩሲያን ግንኙነት በፖለቲካና ምጣኔ ሃብት ረገድም ማጎልበት ይገባል

228

ሰኔ 3/2014 (ኢዜአ)  በቋንቋና ስነ-ጽሑፍ መስክ የዳበረ የኢትዮጵያና ሩሲያን ታሪካዊ ግንኙነት በፖለቲካና ምጣኔ ሀብት ረገድም ማጎልበት እንደሚገባ በቀድሞዋ ሶቪየት ሕብረት የተማሩ ኢትዮጵያዊያን ገለጹ።

በቀዳማዊ ፒተር ዘመን መሰረት የተጣለው የዘመናዊት ሩሲያ ስነ-ጽሑፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ እጅጉን ተቀባይነት ማግኘቱ ይታወቃል፡፡

ሚካኤል ሎሞኖሶቭ፣ አሌክሳንደር ሳስቶኮቭ፣ ኢስማኤል ዘረዘንስኪ፣ አሌክሳንደር ፖተግኒያ፣ ፍሊፕ ፈርቶናተቭ፣ ቪክቶር ቪኖግራደፍ እና መሰል የሩሲያ የሳይንስ፣ የቋንቋና ስነ-ልሳናት ሊቃውንት ደግሞ ለዘመናዊት ሩሲያ ስነ- ጽሑፍ እምርታ ባለውለታዎች ናቸው።

እነዚህ ደራሲዎች በሩሲያኛ ወይም ሞስኮቭኛ ቋንቋ የተጻፉትን ወደ ሌሎች የዓለማችን ቋንቋዎች በመተርጎም እና በሌሎች ቋንቋዎች የተጻፉ ጽሑፎችንም ወደ ሩሲያኛ በመተርጎም ቋንቋው የዓለማችን ዕውቀቶችን እንዲሰንድ አድርገውታል።

ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት /ተመድ/ ስድስት ይፋዊ የሥራ ቋንቋዎች አንዱ የሆነው የሩሲያኛ ቋንቋ ቀን በአዲስ አበባ ሲዘከር በቀድሞዋ ሶቪየት ሕብረት የተማሩ ኢትዮጵያዊያን ተሳታፊዎች ነበሩ።

አቶ አለማየሁ አሊ በዘመነ ደርግ ሩሲያ ከተማሩ 20 ሺህ ኢትዮጵያዊያን መካከል አንዱ ሲሆኑ፤ ለግብርና ሙያ ትምህርት ቢላኩም ከግብርና ሙያቸው ጎን ለጎን በሩሲያ ስነ-ጽሑፍ ፍቅር መለከፋቸውን ይናገራሉ፡፡

በዚህም ዘመን አይሽሬ በሚሰኙ በሩሲያኛ ቋንቋ የተጻፉ የሩሲያ ጥንታዊ ስነ-ጽሑፍ ሥራዎች ሳይቀር በማንበብ አተያይና ተግባቦታቸው እንዲጎለብት በሕይወታቸው ትርጉም ያለው ውጤት እንዲያመጡ ማስቻሉን ይመሰክራሉ።

ኢትዮጵያና ሩሲያ በሃይማኖት፣ በታሪክና በባህል የተቀራረቡ እንደሆኑ ገልጸው፤ በርካታ የኢትዮጵያ ስነ- ጽሑፍ ሀብቶችም ወደ ሩሲያኛ ቋንቋ መተርጎማቸውንና የሞስኮቭኛ መጻህፍትንም ወደ አማርኛ እንደተረጎሙ  ይናገራሉ።

የሩሲያ ስነ-ጽሑፍ ነገረ-አመክንዮ፣ ፍልስፍና፣ ስነ-ልቦና፣ የሳይንስ ዕውቀቶችን መያዙን ገልጸው፤ በኢትዮጵያዊያን ተማሪዎች ዘንድም የሩሲያን ዕውቀት እንዲቀስሙ በጎ ተጽዕኖ እንደነበረው ገልጸዋል።

ቻይናን መሰል አገራት ተማሪዎች ወደ ሩሲያ በማምራት በሳይንስ ዘርፍ ውጤታማ እንደሆኑ በመግለጽ፤ በባህልና ስነ-ጽሑፍ ረገድ የነበረውን የኢትዮጵያና ሩሲያ ግንኙነት በሳይንስ መስክም ማሳደግ ተገቢ ነው ይላሉ።

ለዚህ ደግሞ የተቀዛቀዘውን የኢትዮጵያ ተማሪዎች ወደ ሩሲያ በመላክ ቋንቋን እንዲማሩ ማድረግ ለሁለትዮሽ ግንኙነቱ መዳበር ትልቅ ሚና እንደሚያበረክት ገልጸዋል።

ሩሲያዊያን ከአጼ ምኒልክ ዘመን ጀምሮ ኢትዮጵያን የደገፉ፣ የጤና ተቋም የመሰረቱና የክፉ ቀን ወዳጅ አገር መሆናቸውን ገልፀው፤ ዛሬም በፖለቲካና ኢኮኖሚው ረገድ ግንኙነቱን ወደላቀ ደረጃ ማሸጋገር እንደሚገባ ገልጸዋል።

በተመሳሳይ በቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት መንግስቱ ኃይለማርያም የሩሲያኛ ቋንቋ አስተርጓሚ የነበሩት አቶ በላይ ግርማይ በቀድሞዋ ሶቪየት ሕብረት ሕግ ተምረው በሩሲያ የኢትዮጵያ ኤምባሲና በሌሎች አገሮች ሰርተዋል።

ሩሲያ በቋንቋና ስነ-ጽሑፍ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ አገራት ነጻነት ትልቅ ውለታ ያበረከተች አገር መሆኗን ጠቅሰው፤ በአፍሪካ እና ደቡብ አሜሪካም በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎችን በነጻ ማስተሟሯን ገልጸዋል።

ይህም ከመንግሥታቱ ድርጅት የሥራ ቋንቋዎች አንዱ የሆነው የሩሲያ ቋንቋ እንዲስፋፋ ማድረጉን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በየዘመኑ የገጠማትን ውጫዊ ወረራዎች ስትመክት ሩሲያ ከጎኗ መቆሟን አውስተው፤ በርካታ ኢትዮጵያዊያን በነጻ በማስተማርም ትልቅ ውለታ እንደዋለች ተናግረዋል።

አሁንም የቀደመ የኢትዮ-ሩሲያ የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ እንዲጠናከር በቋንቋ ላይ በስፋት ሊሰራበት ይገባል ነው ያሉት።

'የቋንቋ ዓላማ ሰዎችን ማገናኘት ነው' የሚሉት የአማርኛ ቋንቋን አቀላጥፈው የሚናገሩት በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢያቭገኒ ተርኪን በሩሲያና አማርኛ ቋንቋዎች መሰረታዊ ልዩነት ቢኖርም የሚቀራረቡ ቃላት እንዳሉም ይገልጻሉ።

ታላቁ የሩሲያ ባለቅኔ አሌክሳንደር ፑሽኪን በቅደመ አያቱ ኢትዮጵያዊ የዘር ማንነት እንዳለው አስታውሰው፤

ባለቅኔው በሥራዎቹም ስለኢትዮጵያዊ አያቱ መጻፉን አንስተዋል።

ይህም የኢትዮጵያና ሩሲያን ሕዝቦች የባህል፣ የመንፈስና የስሜት ቅርበት ነጸብራቅ ነው ብለዋል።

ይህ ታሪካዊ የባህል ትስስርና ወዳጅነትም ወደፊት ቀጣይነት እንደሚኖረው በቋንቋ ረገድ በስፋት መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

እስካሁንም በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ሩሲያኛ እንደሚችሉ፣ በሩሲያም አራት ዩኒቨርሲቲዎች አማርኛ ቋንቋን እንደሚያስተምሩ ይገልጻሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም