በመኖሪያ ቤት ግንባታ ወጪ ቆጣቢ እና የፕሮጀክት አስተዳደር ቴክኖሎጂን በመተግበር የተሻለ ሥራ ተከናውኗል

50

ሰኔ 2/2014(ኢዜአ) በበጀት ዓመቱ አሥር ወራት በመኖሪያ ቤት ግንባታ ወጪ ቆጣቢ እና የፕሮጀክት አስተዳደር ቴክኖሎጂን በመተግበር የተሻለ ሥራ መከናወኑን የከተማና መሰረተ-ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገለጹ።

ምክርቤቱ በዛሬ ውሎው የከተማና መሰረተ-ልማት ሚኒስቴርን የ2014 በጀት ዓመት የአሥር ወር የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ገምግሟል።

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ዋና ኦዲተር እና ምክትል ዋና ኦዲተር አበራ ታደሰን ሹመትም በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።

የከተማና መሰረተ-ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ፤ በበጀት ዓመቱ የተሻሻለ የመኖሪያ ቤት ግንባታን ለማፋጠን ወጪ ቆጣቢ እና የፕሮጀክት አስተዳደር ቴክኖሎጂን በመተግበር የተሻለ ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል።

በአሥሩ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባና ድሬደዋ ከተማ አስተዳደሮች በማህበራት፣ በሽርክና እንዲሁም በግለሰብ ደረጃ ከ95 ሺህ በላይ ቤቶችን ለመገንባት ታቅዶ ከ91 ሺህ በላይ ቤቶች መገንባታቸውን ጠቅሰዋል።

በመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት ከ20 ሺህ በላይ ቤቶችን ለመገንባት የተያዘው እቅድ የማስተግበሪያ ደንብና መመሪያዎች ባለመፅደቃቸው ሳይፈጸም መቅረቱን ተናግረዋል።

መንግሥት በጀመረው የጋራ መኖሪያ ቤት ልማት መርሃ-ግብር  እንዲገነቡ እቅድ የተያዘላቸው  22 ሺህ 753 ቤቶች በፋይናንስ እጥረት ግንባታቸው አለመከናወኑንም አንስተዋል።

ከተመዘገቡ ቤት ፈላጊዎች ከ49 ቢሊዮን ብር በላይ እንዲቆጥቡ ለማድረግ ቢታቀድም 5 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ብቻ መሳካቱን አስረድተዋል።

በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በነበረው ጦርነት የተጎዱ 78 ከተሞችን መልሶ ለመገንባት ‘የቁርጥ ቀን የከተሞች ጥምረት’ በመመስረት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሚኒስቴሩም ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብና የዓይነት ድጋፍ ማድረጉን አብራርተዋል።

ሚኒስትሯ በሪፖርታቸው በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ነባር መንገዶችን ለማጠናከርና ደረጃ ለማሻሻል እንዲሁም አዳዲስ መንገዶችን ለመገንባት የተያዘው እቅድ አፈጻጸሙ ዝቅተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባላት በበኩላቸው፤ ከቤቶች ልማትና መንገድ ግንባታ አንጻር የተያዘው እቅድ አለመሳካቱን ተችተዋል።

በቀጣይ ሚኒስቴሩ እቅዱን ለማሳካትና ሕብረተሰቡን ፍትሃዊ ተጠቃሚ ለማድረግ በልዩ ትኩረት እንዲሰራ አሳስበዋል።

ሚኒስትሯም በቀጣይ በመንገድ ግንባታ  ክልልን ከክልል እንዲሁም ለቀጣናዊ ትስስር ፋይዳ ያላቸው መንገዶች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

ክልሎችም አቅማቸውን በማሳደግ የወረዳና ዞን አገናኝ መንገዶችን እንዲሰሩ ይደረጋል ነው ያሉት።  

የቤት ችግርን ለመፍታት የግሉን ዘርፍ በማሳተፍ ቤቶችን ለማልማት እንደሚሰራም ነው የተናገሩት።

የከተማ መሰረተ-ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሸዊት ሻንካ፤ ከተሞች ያሉባቸውን ችግሮች ለመፍታት የተጀመሩ ሥራዎች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በአሥር ዓመት የልማት እቅዱ በየዓመቱ 400 ሺህ ቤቶችን ለመገንባት ቢታቀድም የ2014 በጀት ዓመት አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለቤት አልሚዎች ምቹ ሁኔታን በመፍጠር በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 12ኛ መደበኛ ስብሰባ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ዋና ኦዲተር መሰረት ዳምጤ እና ምክትል ዋና ኦዲተር አበራ ታደሰን ሹመት በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።