በጋምቤላ ክልል ሦስተኛው ዙር የኮቪድ-19 በሽታ መከላከያ ክትባት መስጠት ተጀመረ

370

ጋምቤላ ሰኔ 2/2014(ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል ከ182 ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች የኮቪድ-19 በሽታ መከላከያ ክትባት በዘመቻ መስጠት መጀመሩን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ታች ኮንግ ክትባቱን ሲያስጀመሩ እንዳሉት ክትባቱ የሚሰጠው ጋምቤላ ከተማ መስተዳድርን ጨምሮ በክልሉ በሚገኙ 14 ወረዳዎችና በሰባት የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ነው።

ክትባቱ የሚሰጠው በሁሉም የጤና ተቋማትና በጊዜያዊ የክትባት መስጫ ጣቢያዎች መሆኑንም ገልጸዋል።

የክልሉ ሕዝብ በጤና ተቋማቱና በክትባት መስጫ ጣቢያዎች የሚሰጠውን ክትባት በመውሰድ በሽታውን እንዲከላከል ምክትል ኃላፊው ጥሪ አቅርበዋል።

የቢሮው የእናቶችና ህፃናት ጤና ዳይሬክተር አቶ ኡጁሉ ኡሞድ በክልሉ ለሶስተኛ ዙር በሚሰጠው የኮቪድ 19 መከላከያ ክትባት እድሜያቸው ከ12 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

ለዘመቻው ከተዘጋጀው 182 ሺህ ዶዝ ክትባት ሲሆን፣40 ከመቶ የሚሆነው ለስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች አገልግሎት እንደሚውል ገልጸዋል።

በክልሉ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዙሮች በተሰጠው የኮቪድ 19 ክትባት 153 ሺህ የሚሆኑ ሰዎችን ለመከተብ ታቅዶ በአማካይ 94 ከመቶ ማሳካቱን ተናግረዋል።

በክትባት ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ ክትባቱን ከወሰዱ ሰዎች መካከል አቶ ኩዊች ውዊው በሰጡት አስተያየት እንደ ሀገር ብሎም እንደ ክልል የኮሮና ቫይረስ እያደረሰ ያለውን የጤና ችግር ለመከላከል ክትባቱን መውሰዳቸውን ገልጸው፤ ሕዝቡም ክትባቱን በመውሰድ ተጠቃሚ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

ክትባቱን ለሁለተኛ ጊዜ መውሰዳቸውንና ምንም ዓይነት ችግር እንዳላስከተለባቸው የገለጹት ደግሞ አቶ ደረጀ ሙራድ ናቸው።

ኅብረተሰቡ ክትባቱን በመውሰድ  ጤንነቱን እንዲንከባከብ መክረዋል።

በክልሉ በ36 ሺህ ሰዎች ላይ በተካሄደ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ 1 ሺህ 820  ሰዎች በበሽታው ተይዘው መገኘታቸውንና ከመካከላቸው 26 ሰዎችም ለሞት መዳረጋቸውን የቢሮው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም