በክልሉ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን ለማበረታታት የተለያዩ እቃዎች ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ ተደርጓል

350

ጎንደር (ኢዜአ) ሰኔ 2/2014 በአማራ ክልል የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን ለማበረታታት ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው እቃዎች ከቀረጥ ነጻ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ መደረጉን በጉምሩክ ኮሚሽን የባህር ዳር ቅርንጫፍ አስታወቀ፡፡

ቅርንጫፉ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ለባለድርሻ አካላት ያዘጋጀው የምክክር መድረክ ዛሬ በጎንደር ከተማ ተካሂዷል።

የቅርንጫፉ የጉምሩክ ኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ሸምሱ ጀማል እንደተናገሩት፣ ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ ከተፈቀዱ እቃዎች መካከል የግንባታና የማምረቻ ማሽነሪዎች ይገኙበታል።

ለሆቴልና ቱሪዝም አገልግሎት የሚውሉ ዘመናዊ የመገልገያ እቃዎችን ጨምሮ የህዝብ መጓጓዣ ተሽከርካሪዎችና ሌሎች ኢንቨስትመንቱን ለማበረታታት የሚያስችሉ መለዋወጫዎች እንደሚገኙባቸው ገልፀዋል።

አቶ ሸምሱ እንዳሉት ከቀረጥ ነጻ የማበረታቻ ስርአቱ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል በአግሮ ፕሮሰሲንግ የተሰማሩ አምራች ኢንዱስተሪዎችና አገልግሎት ሰጪ የግልና የመንግስት ተቋማት ይጠቀሳሉ።

በተጨማሪም በግሉ ዘርፍ በሆቴልና ቱሪዝምና በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩ 83 የግል ባለሃብቶች ከቀረጥ ነጻ አገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከቀረጥ ነጻ አገልግሎቱ የተሰጠው ባለፉት 10 ወራት መሆኑን የጠቆሙት ምክትል ሥራ አስኪያጁ፣ "ንብረቶቹ ከገቡበት አላማ ውጪ ወደ ሦስተኛ ወገን እንዳይተላለፉ ቁጥጥርና ክትትል እየተደረገ ነው" ብለዋል፡፡  

"ቅርንጫፉ የአገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋና ተደራሽ በማድረግ በኩል በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራሮችን እየተገበረ ነው" ያሉት ደግሞ የቅርንጫፉ ሥራ አስኪያጅ አቶ አለነ መሃሪ ናቸው፡፡

በተለይ ወረቀት አልባ የጉምሩክ አሰራሮችን በመተግበር የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ባህል ከማዳበር ባለፈ ውጤታማ የተገልጋዮች የመረጃ ልውውጥ ስርአት መፍጠር መቻሉን አስረድተዋል።

የክልሉን የኤክስፖርት ዘርፍ በማሳለጥ በኩል የጉምሩክ ቅርንጫፎች ቅዳሜና እሁድን ጨምሮ በበአላት ወቅት የሚሰሩበት ሁኔታ እንዲመቻች ያሳሰቡት ደግሞ የመድረኩ ተሳታፊ አቶ ገዛኸኝ ሞላ ናቸው፡፡

ሌላው የመድረኩ ተሳታፊ አቶ አዱኛ አያሌው በበኩላቸው፣ የጉምሩክ የአገልግሎት አሰጣጥ በየጊዜው እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል።

"የምክክር መድረኩም ተገልጋዮች ግዴታና መብቶቻቸውን በሚገባ እንዲገነዘቡ ያስቻለ ነው" ብለዋል።

በምክክር መድረኩ ላይ የክልሉን አመራሮች ጨምሮ አስመጪዎችና ላኪዎች፣ የጉምሩክ አስተላላፊዎች፣ ባለሀብቶች እንዲሁም አጋርና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም