በዞኑ በአርሶ አደሮች የተዘጋጀ ኮምፖስት ለመኸር ሰብል ልማት ጥቅም ላይ እየዋለ ነው

435

ደብረ ማርቆስ ሰኔ 2/2014 (ኢዜአ) በምስራቅ ጎጃም ዞን በአርሶ አደሮች የተዘጋጀ ከ5 ሚሊዮን የሚበልጥ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለመኸር የሰብል ልማት ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ሃላፊ አቶ ፈንታሁን ቸኮል ለኢዜአ እንደተናገሩት፣ በአሁኑ ወቀት የተከሰተውን የፋብሪካ ሰራሽ ማዳበሪያ እጥረት በተፈጥሮ ማዳበሪያ በመተካት ምርትማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው።

በዚህም በመደበኛውና በንቅናቄ ከ6 ሚሊዮን ሜትር ኩዩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

እስካሁንም ከ5 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ የሚሆነው ማዳበሪያ በ226ሺህ ሄክታር ማሳ ላይ በማስገባት ከአፈሩ ጋር እንዲብላላ እየተደረገ መሆኑን ተናግርዋል።

ቀሪው የተፈጥሮ ማዳበሪያ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ማሳ ላይ እንደሚበተን ጠቁመው፣ ቨርሚን ኮምፖስትም በአርሶ አደሩ እየተዘጋጀ መሆኑን ገልፀዋል።

እንደ ሃላፊው ገለጻ፣ በዚህ ዓመት የተፈጥሮ ማዳበሪያ የተበተነበት ማሳ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ80 ሺህ ሄክታር በላይ ብልጫ አለው።

ዘንድሮ እየተስተዋለ ያለውን የሰው ሰራሽ ማዳበሪያ አቅርቦት እጥረት በራስ አቅም ለመሸፈን አርሶ አደሩ በዘመቻ ጭምር ማዳበሪያ አዘጋጅቶ እንዲጠቀም መደረጉ ለታየው እድገት  ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም የተፈጥሮ ማዳበሪያ የመሬት ለምነትን ጠብቆ በማቆየት ምርታማነትን ለመጨመር ያለውን ጠቀሜታ አርሶ አደሩ መገንዘቡ ሌላው ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል።

የአዋበል ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ሙቀትሰው ዋሴ እንዳሉት፣ በአንድ ሄክታር ማሳ ላይ ኮምፖስት በመጨመር በቆሎ ለመዝራት የዝናብ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ዘንድሮ ከ85 ኩንታል በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘጋጅተው እየተጠቀሙ መሆኑንና ጠቅሰዋል።

"የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማዳበሪያ ግዢ የሚወጣውን ወጪ ከመቀነስ ባለፈ ምርታማነትን ስለሚያሳድግ ዘንድሮ መጠኑን ከፍ በማድረግ አዘጋጅቺያለሁ" ብለዋል።

"ከ100 ኩንታል በላይ ኮምፖስት አዘጋጅቼ ሁለት ሄክታር በሚጠጋ ማሳ ላይ በትኛለሁ" ያሉት ደግሞ የማቻከል ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ባድማው እይላቸው ናቸው።

በምርት ዘመኑ ከ6 ኩንታል በላይ ሰው ሰራሽ ማዳበሪያ እንደሚያስፈልጋቸው ጠቅሰው፣ እስካሁን ድረስ አንድ ኩንታል ተኩል ብቻ መግዛታቸውን ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ ለተፈጥሮ ማዳበሪያ ትኩረት በመስጠትና በጥራት በማዘጋጀት አስካሁን የከፋ ችግር እንዳልገጠማቸው የናግረዋል።

በዞኑ በ2014/15 የምርት ዘመን በመኽር ከሚሸፈነው 611 ሺህ ሄክታር ማሳ ከ26 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ከመምሪያው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም