የመንግስትና የግል ተቋማት ሰራተኞችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የማህበራዊ ጤና መድህን አገልግሎ ተግባራዊ ይደረጋል

2

አዳማ ሰኔ 2/2014 (ኢዜአ ) በአዲሱ የበጀት ዓመት የመንግስት ሰራተኞችን፣ ጡረተኞችና በግል ተቋማት ድርጅቶች የማህበራዊ ጤና መድህን አገልግሎትን ተግባራዊ እንደሚደረግ የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት አስታወቀ።

በአዲሱ የበጀት ዓመት የማህበራዊ ጤና መድህን አገልግሎት ለማስጀመር በሚቻልበት ሂደት ላይ በአዳማ ከተማ ከባለድርሻ አካላትጋር ውይይት እየተደረገ ነው።

የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍሬህይወት አበበ እንደገለፁት የመንግስት ሰራተኞችን ጨምሮ ጡረተኞች፣ በግል ተቋማትና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የማህበራዊ ጤና መድህን ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል።

የማህበራዊ ጤና መድህን ስርዓት በሀገሪቱ አለመጀመሩን የጠቀሱት ዳይሬክተሯ፣ በአሁኑ ወቅት ከጤና ሚኒስቴርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የአተገባበር ፎኖተ ካርታ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

በተለይ በቀጣይ 10 ዓመት ሁሉም ዜጎች የጤና መድህን አገልግሎት ሽፋን እንዲኖራቸው ግብ ተቀምጦ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የመድረኩ ዓላማ የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞ፣ የመምህራን ማህበርና ሌሎች ባለድርሻ የማህበራዊ ጤና መድህን ለማስጀመር የተዘጋጀው ዕቅድ በግብዓት እንዲያዳብሩና በአተገባበሩ ላይ ግልጽ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማስቻል መሆኑንም አመልክተዋል።

“መደበኛ ባልሆነ የኢኮኖሚ መስክ ላይ ያሉትን አርሶ አደርና አርብቶ አደሩን ተጠቃሚ ያደረገ ማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አበረታች ውጤት የተገኘበት በመሆኑ ማህበራዊ ጤና መድህን ለመተግበር ተሞክሮ ተገኝቷል” ብለዋል።

በሀገሪቷ ከ800 በላይ ወረዳዎች የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን እየተተገበረ መሆኑን ጠቅሰው በዚህም 44 ሚሊዮን ዜጎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በመድረኩ ላይ የመወያያ ጽሑፍ ያቀረቡት የዋና ዳይሬክተሯ አማካሪ አቶ አብዱልጀሊል ጀማል  በአሁኑ ወቅት የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ዋጋ  እየናረ በመምጣቱ ማህበራዊ የጤና መድህን ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ ነው ብለዋል።

መንግስት ከሚመደበው በጀት ውጪ ግለሰቦች ከኪሳቸው በዓመት ከ39 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ እያወጡ መሆኑን በ2014  ዓ.ም በተካሄደው ጥናት መረጋገጡን ጠቅሰዋል።

በህክምና ቁሳቁስና የመድኃኒት የዋጋ ንረት ምክንያት ዜጎች ተገቢውን አገልግሎት እያገኙ ባለመሆኑ ማህበራዊ የጤና መድህን ተግባራዊ ማድረግ ማስፈለጉን አመላክተዋል ።