በሀገሪቱ የምግብና ስርአተ ምግብ ትግበራን ለማፋጠን የሚያስችል ስትራቴጂ ተቀርፆ እየተሰራ ነው – የጤና ሚኒስቴር

1

ሀዋሳ ሰኔ 02/2014 (ኢዜአ)በሀገሪቱ የምግብና የስርአተ ምግብ ትግበራን ለማፋጠን የሚያስችል ስትራቴጂ ተቀርፆ እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ብሄራዊ የምግብና ስርአተ ምግብ እስትራቴጂና የሲዳማ ክልል የምግብና የስርአተ ምግብ ጉባዔ  ማብሰሪያ መድረክ ዛሬ በሀዋሳ ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ  የምግብና የስርአተ ምግብ ችግር እየተስተዋለ ይገኛል።

በመሆኑም መንግስት ችግሩን ለመፍታት የተለያዩ ሴክተሮችንና አጋር ድርጅቶችን እንዲሁም ማህበረሰቡን በማስተባበር የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን ገልፀዋል።

ከነዚህ ተግባራት መካከል የብሄራዊ ስርአተ ምግብ ፕሮግራም አብይ ኮሚቴን እና የቴክኒክ ኮሚቴን ከክልል እስከ ወረዳና ቀበሌ በማደራጀት ትግበራውን እያስተባበረና እየመራ መቆየቱን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን የክትትል ግምገማና ጥናት እንዲሁም የምግብ ማበልፀጊያ ኮሚቴዎችን በማደራጀት ለትግበራው የሚያግዙ ስራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።

በተለይ ከሰቆጣ ቃል ኪዳን የሙከራ ትግበራ የተገኘዉን ተሞክሮ በመቀመር በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በተደረገዉ እንቅስቃሴ የብሄራዊ ስርአተ ምግብ ትግበራዉን በስኬት ማጠናቀቅ መቻሉን ነዉ ያስታወቁት።

አሁን ላይም በፌዴራል እና ክልል ደረጃ በፊት የነበረዉን የብሄራዊ ስርአተ ምግብ አስተባባሪ አብይ ኮሚቴ በሚያጠናከር መልኩ የምግብና ስርአተ ምግብ ጉባዔን በየደረጃዉ ማቋቋም ማስፈለጉን አመላክተዋል።

ይህንን እዉን ለማድረግ የሚያስችለዉ ብሄራዊ ስትራቴጂዉ በዛሬዉ መድረክ ላይ ይፋ መደረጉንም አስታዉቀዋል።

የሰቆጣ ቃል ኪዳን የፕሮግራም ማስፈፀሚያ ማናጀር ዶክተር ሲሳይ ሲናሞ በበኩላቸዉ መቀንጨር በሀገር ላይ የሚያስከትለዉ ጉዳት በገንዘብ ሲሰላ በዓመት 55 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር መሆኑ በጥናት መረጋገጡን ጠቁመዋል።

ሀገራዊ የመቀንጨር ምጣኔም 6 ሚሊዮን መሆኑን ነዉ የተናገሩት።

የመቀንጨር ችግርን ለመከላከል በአማራ ክልል በተካሄደዉ የሙከራ ምእራፍም በአጭር ግዜ ዉስጥ ከ51 በመቶ ወደ 43 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም እንደ ሀገር 7 ነጥብ 8 ሚሊየን ህፃናትን ከመቀንጨር ለመታደግ በ240 ወረዳዎች እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

መቀንጨር በህፃናት አእምሮ እድገት ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማስከተል የትምህርት መቀበል ፈጠራና ምርታማነት ላይ ተፅእኖ ስለሚያሳድር ችግሩን ለመቅረፍ የሁሉንም ተሳትፎ እንደሚጠይቅም አስገንዝበዋል።

የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሰላማዊት መንገሻ በበኩላቸው በክልሉ የመቀንጨር ችግርን ለመከላከል በተመረጡ 10 ወረዳዎች እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ይህንን ስራ ለማፋጠን የክልሉ የምግብና የስርአተ ምግብ ጉባዔ ዛሬ መመስረቱን ገልፀዋል።

የጉባዔው መመስረትም በቀጣዮቹ አምስት አመታት በክልሉ 351 ሺህ ህፃናትን ከመቀንጨር ችግር ለመታደግ ምቹ መደላድል ይፈጥራል ባይ ናቸዉ።

እንደ ሀገር የመቀንጨር ችግርን ለመከላከል በዚህ አመት ብቻ 500 ሚሊዮን ብር ተመድቦ አየተሰራ መሆኑ ታውቋል።