የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ እና ፀሐይ አሳታሚ ድርጅት የጥናትና ምርምር ስራዎችን ሰንዶ ተደራሽ ለማድረግ በጋራ ለመሥራት ተስማሙ

6

ሰኔ 02 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ እና ፀሐይ አሳታሚ ድርጅት የጥናትና ምርምር ስራዎችን ሰንዶ ዓለም አቀፍ ተደራሽ እንዲሆኑ ለማድረግ በጋራ ለመሥራት የሚያስችል የጋራ ስምምነት ተፈራረሙ።

የመግባቢያ ስምምነቱን የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጽጌ ገብረማርያም እና የፀሐይ አሳታሚ ድርጅት ባለቤት ኤሊያስ ወንድሙ ተፈራርመዋል።

የአካዳሚው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጽጌ ገብረማርያም፤ ስምምነቱ አካዳሚው በተፈጥሮና ማህበራዊ ሳይንስ እውቀትን ሰንዶ ለኅብረተሰቡ ለማድረስ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ያሉ በርካታ የሥልጣኔ፣ የባህልና የእውቀት መገለጫዎች በምሁራን ተጽፈው በተለያዩ ቋንቋዎች ታትመው በመላው ዓለም ለንባብ እንዲበቁ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ ሁለቱ ተቋማት ያደረጉት ስምምነት በተፈጥሮና ማህበራዊ ሳይንስ እውቀትን ሰንዶ ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ በቅርቡ የጀመረውን የሳይንስና ቴክኖሎጂ መዝገበ-ቃላት ወደ ተለያዩ ቋንቋዎች በመተርጎም ለማስተማር በጋራ እንደሚሰሩም ገልጸዋል።

የፀሐይ አሳታሚ ድርጅት ባለቤት ኤሊያስ ወንድሙ፤ ድርጅታቸው ከአካዳሚው ጋር ስምምነት ማድረጉ በአገር ውስጥና በውጭ አገር የሚኖሩ ምሁራንን ለማሳተፍ ያግዛል ብለዋል።

የነገዋን ኢትዮጵያ ለሚቀጥለው ትውልድ ለማቆየት በጋራ የተሻለ ሥራ መሥራት አስፈላጊ ስለመሆኑም አብራርተዋል።

በተለያዩ ህትመቶች ላይ የሚሰተዋለውን የጥራት ችግር ለማስተካከል፣ የመጻሕፍት አርትኦት ለመሥራትና ሌሎች ተግባራትን በጋራ ለማከናወንም ስምምነቱ አስፈላጊነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ በተለያየ ዘርፍ ጥናትና ምርምር የሚያደርጉ 200 ምሁራንን በአባልነት ያቀፈ መሆኑ ታውቋል።