ካምብሪጅ አካዳሚ ከ700 በላይ መጻሕፍት ለአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት አበረከተ

58

ሰኔ 2 ቀን 2014 (ኢዜአ)ካምብሪጅ አካዳሚ የተለያዩ ይዘት ያላቸው ከ700 በላይ መጻሕፍት ለአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት አበረከተ።

ለአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት “ሚሊዮን መጻሕፍት ለሚሊኒየሙ ትውልድ” በሚል መሪ ኃሳብ የመጻሕፍት ማሰባሰብ ንቅናቄ የተለያዩ ተቋማት ምላሽ እየሰጡ ነው።

ይህንንም ተከትሎ የካምብሪጅ አካዳሚ የተለያዩ ይዘት ያላቸው ከ700 በላይ መጻሕፍትን ለአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት በዛሬው ዕለት አስረክቧል።

የካምብሪጅ አካዳሚ ፕሬዝዳንት ዶክተር ገመቺስ ደስታ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ትምህርት ቤቱ መጻሕፍቱን ድጋፍ ያደረገው መጻሕፍት ገዝቶ ነው።

መጻሕፍቱም የሳይንስ፣ የሂሳብ፣ የአስተዳደር፣ የቴክኖጂና ሌሎች ዘርፎች ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሁሉም ትምህርት ቤቶች ለልጆቻቸው ማካፈልን ለማስተማር ለአብርሆት ቤተ መጽሃፍት የበኩላቸውን ሊያበረክቱ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በቀጣይ አካዳሚው 25 ሺህ መጻሕፍት ለአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት ለማበርከት ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም የአካዳሚው ፕሬዝዳንት ተናግረዋል።

መጻሕፍቱን የተረከቡት የአብርሆት ቤተ-መጻህፍት ዋና ሃላፊ ኢንጅነር ውባየሁ ማሞ በበኩላቸው ትምህርት ቤቱ ላበረከተው መጻህፍት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ድጋፉ ትምህርት ቤቶች ካላቸው መጻሕፍት ውስጥ ለሌሎች ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው የሚያስተምርና ሌሎችም ይህንን አርአያ መከተል እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

መጻሕፍት የማሰባሰቡ መርሃ ግብር ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የማሰባሰቢያ ጊዜው እንዲራዘም መደረጉን ገልጸዋል።

በእነዚህም ቀናት ተቋማትና ግለሰቦች የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።