የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ አለማቀፍ ችግር የሆነውን አየር ንብረት ለውጥ ለመቆጣጠር ትልቅ ሚና አለው -- የዘርፉ ምሁራን

489

ሀዋሳ ሰኔ2/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አለማቀፍ ችግር እየሆነ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥን ለመቆጣጠር አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን የዘርፉ ምሁራን አመለከቱ ፡፡

በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የደንና ተፈጥሮ ሃብት ኮሌጅ መምህራንና ተመራማሪዎች ለኢዜአ እንደገለጹት በሀገሪቱ እየተካሄደ ያለው የአረንጋዴ አሻራ መርሃግብር ለዘርፍ መማር ማስተማር እገዛው የጎላ ነው፡፡

በኮሌጁ መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር መሰለ ነጋሽ ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ መንግስት በከፍተኛ ሃላፊነት በዘርፉ እያከናወነ ያለው ተግባር የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አለም አቀፍ አጀንዳ ለሆነው የአየር ንብረት ለውጥ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ፕሮግራም እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዘርፉ የምታከናውነው ተግባር በበርካታ የአለም ሀገራት እውቅና እያገኘና ስራውን በቅርበት የመከታተል ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

የደን ልማቱ በየአካባቢው ያሉ ተፋሰሶችን እንዲለሙ በማድረግ ጎረቤት ሃገራትን ጭምር ተጠቃሚ የሚያደርገውን የአባይ ተፋሰስ ለመጠበቅ የሚረዳ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡

በዘመቻ የሚያከናወነውን ተግባር በባለሙያ ማስደገፍ፣ ተቋማዊ አሰራርን መከተል፣ የተቀናጀና የተጠናከረ መረጃ ስርዓት እንዲኖረው ማድረግ ከተቻለ በአጭር ጊዜ ውስጥ በዘርፉ ትልቅ ውጤት እንደሚመዘገብም ተናግረዋል፡፡

ለውጤቱ የመንግስት አካላት፣የምርምርና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

እንደሀገር የተጀመረውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ማስቀጠል ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አቅምን የሚያጎለብትና ስነምህዳሩ እንዲጠበቅ በማድረግ ምርታማነትን እንደሚጨምርም ገልጸዋል፡፡

ኮሌጁ በዘርፉ የተማረ የሰው ሃይል ለማፍራት በሚያከናውነው ተግባርና የተለያዩ የምርምር ስራዎችን ለማከናወን በሚያደርገው ጥረት መንግስት የጀመረው ስራ እንደሚያግዘውም ተናግረዋል፡፡

በኮሌጁ የጥርም ደን ግብርና ትምህርት ክፍል ሃላፊና መምህር ወይዘሮ ገነት ነጋሽ በበኩላቸው ዝናብን መሰረት ያደረገ ግብርና እንደሚተገብር ሀገር አረንጓዴ አሻራ የህልውና ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡

በዘርፉ ቀጣይነት ያለውን ተግባር በማከናወን ግብርናውን ማገዝና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

ከሳይንሱ ባሻገር አርሶ አደሩ ዘንድ በርካታ ተሞክሮዎች መኖራቸውን የገለጹት መምህርቷ በዘርፉ የሚመረቁ ምሁራንም ማህበረሰቡ ዘንድ በመውረድ በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገው ጥረት እንዲሳካ አካባቢን የመጠበቅ ልምድን ማዳበር እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ የአየር ንብረት ለውጡን ለመቋቋም፣ለግብርና ምርታማነት ለብዝሃ ህይወት መጠበቅ ሚናው ከፍተኛ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ  በኮሌጁ የደን አጠባበቅና አያያዝ ትምህርት ክፍል ሃላፊና መምህር ዘላለም ታደለ ናቸው፡፡

የደን ሳይንሱ ቶሎ ውጤት የሚገኝበት ዘርፍ አለመሆኑን ገልጸው ያለፉት ዓመታት ስራም በቀጣዮቹ አምስትና አስር ዓመታት ውስጥ ተጨባጭ ለውጥ ይታይበታል ብለዋል፡፡

ከተከላው ባለፈ እንክብካቤ ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ባለሙያዎቹ እንዳሉት እንደሀገር ላለፉት ዓመታት ሲካሄዱ የዘመቻ የተከላ ሂደቶች ባለቤት እንዲኖራቸው በማድረግ ተገቢውን እንክብካቤ ሊያገኙ ይገባል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም