ሴቶች አቅማቸውን በማውጣት የአገር ብልፅግናን እውን ማድረግ እንዳለባቸው ተገለፀ

4

ጭሮ ሰኔ 2/2014 (ኢዜአ) ሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎአቸውን በማጠናከር የኢትዮጵያን ብልፅግና እውን የማድረግ ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው የምዕራብ ሀረርጌ ዞን ሴቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ገለፀ፡፡

የኦሮሚያ ክልል የስራ ሃላፊዎች፣ የዞኑ አመራሮችና ሴቶች ሊግ አባላት የተሳተፉበት የዞኑ ሴቶች ሊግ ኮንፈረንስ በጭሮ ከተማ ተካሄዷል፡፡

የምዕራብ ሀረርጌ ዞን ሴቶች ሊግ ኃላፊ ወይዘሮ ወዚራ አህመድ በኮንፈረንሱ ላይ እንዳሉት የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ “ሴቶች አይችሉምን አመለካከት” መለወጥ ተችሏል፡፡

ሴቶች በኢኮኖሚ፣ በማህራዊና በፖለቲካው ዘርፍ አቅማቸውን በማውጣትና ተደጋግፈው በመስራት   ብልፅግናን በማረጋገጥ ውስጥ ሚናቸውን መወጣት አለባቸው ብለዋል፡፡

የኦሮሚያ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊና የእለቱ የክብር እንግዳ ወይዘሮ ሳሚያ አብደላ በበኩላቸው ሀገሪቱ ከገጠሟት ችግሮች ተላቃ ወደ ሰላምና ልማት ለማሻገር በሚደረገው ጥረት ውስጥ “ሴቶች ወሳኝ ሚና አላቸው”፡፡

በመሆኑም አለመግባባቶችና ግጭቶች ተወግደው ሰላም እንዲሰፍንና ልማት እንዲስፋፋ ሴቶች በሁሉም ዘርፍ ሚናቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

በአመራርነት ቦታ ያሉትም ሴቶች የተሰጣቸውን ስራ በአሸናፊነት በመወጣት አቅማቸውን ማሳየት እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

“ከገመቺስ ወረዳ ኮንፈረንሱ ላይ የተገኙት ወይዘሮ መስከረም ገዙ ሴቶች በየዘርፉ በአመራርነትና በባለሙያነት ተሰማርተን እንድንሰራ የተሰጠንን እድል ለሀገርና ህዝብ ውጤታማ ስራ በመስራት ማስመስከር አለብን” ብለዋል፡፡

በኮንፈረንሱ ላይ የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ላይ ሰፊ ውይይት ማድረጋቸው በያሉበት አካባቢ ያሉ ሴቶችን ለማነቃቃት ያነሳሳቸው መሆኑን አክለዋል፡፡

ከሚኤሶ ከተማ ኮንፈረንሱ ላይ የተሳተፉት ወይዘሮ አዚዛ አህመድ በበኩላቸው ኮንፈረንሱ ሴቶች ወደ አንድነት መጥተን ሀገርን በማልማት ጉዳይ መሬት የሚወርድ ስራ እንድንሰራ አደራ ሰጥቶናል ነው ያሉት፡፡

“ሴቶች ከእናትነት በተጨማሪ በማህበራዊ ጉዳዮችም ጠንካራ ስራ በመስራት የሀገራችንን ብልፅግና እናረጋግጣለን” ሲሉ ወይዘሮ አዚዛ ቁርጠኝነታቸውን ገልፀዋል፡፡