በሁለቱ ክልሎች ከ480ሺህ በላይ ሰዎችን ተደራሽ የሚያደርገው 3ኛው ዙር የኮሮና ቫይሬስ መከላከያ ክትባት ዛሬ ተጀመረ

10

ሰመራ/አሶሳ ሰኔ 02 / 2014(ኢዜአ) በአፋርና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ከ480 ሺህ በላይ ሰዎች የሚከተቡበት ሶስተኛው ዙር የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባት ዛሬ ተጀመረ፡፡

ዛሬ በተጀመረው ዘመቻ በአፋር ክልል 300 ሺህ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ደግሞ ከ182 ሺህ በላይ ሰዎች ይከተባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የየክልሎቹ ጤና ቢሮዎች አመራሮች አስታውቀዋል፡

በአፋር ክልል  የሚካሄደውን ዘመቻ የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ውቲካ ኑሪ በሎግያ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተገኝተው አስጀምረውታል።

ለአሥር ቀናት  በሚቆየው በዚሁ ዘመቻ  ክትባቱ በጤና ተቋማት በተመረጡ ቦታዎችና ቤት ለቤትም ጨምሮ ዕድሜያቸዉ ከ12 ዓመት በላይ ለሆኑ ዜጎች ይሰጣል ብለዋል።


የሎግያ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ፋጡማ ሸሄም ክትባቱ ጤናማ ህይወት ለመምራት እንደሚያግዛት ገልጻለች።

ሌላው የዚሁ ትምህርት ቤት ተማሪ  ዓሊ ኢሴ በበኩሉ ክትባቱ የራሱንና የቤተሰቡን ጤና ለመጠበቅ እንደሚያስችለው ገልጿል።

በአፋር ክልል በሁለት ዙሮች የኮሮና መከላከያ ክትባት ከ54ሺህ በላይ ሰዎች መሰጠቱን የክልሉ ጤና ቢሮ መረጃ ያመለክታል።

በተመሳሳይ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጤና ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዋጮ ወቡልቾ በዘመቻው ለ182 ሺህ 283 ሰዎች ክትባት ለመስጠት ታቅዶ መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡

ክትባቱ በአሶሳና መተከል ዞኖች በሚገኙ ጤና ተቋማትና የክትባት መስጫ ጊዜያዊ ማዕከሎች እንዲሁም በአራት የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ይሰጣልም ብለዋል፡፡

ክትባቱን ለመስጠት 2 ሺህ 200 የሚጠጉ የጤና ባለሙያዎችና አስተባባሪዎች እንደተሰማሩም አቶ ዋጮ ተናግረዋል፡፡

ከክትባቱ በተጓዳኝ ህብረተሰቡ እራሱን ከቫይረሱ እንዲጠብቅ ቅስቀሳ ይደረጋል ብለዋል፡፡

በአሶሳ ከተማ ክትባቱን የወሰዱት ወይዘሮ ዘብሽወርቅ ታደለ ህብረተሰቡ “የኮሮና በሽታ ጠፍቷል” በሚል የሚያሳየው መዘናጋት አግባብ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡

ክትባት ያልወሰዱትን በመቀስቀስ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡም በማከል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 64 ሺህ 900 በላይ ሰዎች ተመርምረው ከ5 ሺህ 200 በላይ ቫይረሱ ሲገኝባቸው የ41 ሰዎች ህይወት ማለፉን ከቢሮው የተገኘ መረጃ አመልክቷል፡፡